Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ በፍርድ ቤቶች በተደረጉ ክርክሮች ከ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የሕዝብና መንግሥት ጥቅም ማስከበር ተቻለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ በፍርድ ቤቶች በተደረጉ ክርክሮች ከ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የሕዝብና መንግሥት ጥቅም ማስከበር ቻለ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ክርክር የፍርድ ቤት ውሳኔ ካገኙ 1 ሺህ 491 መዝገቦች ውስጥ 1 ሺህ 382 መዝገቦች ለአስተዳደሩ ተወስኗል።

በዚህም 3 ቢሊየን 212 ሚሊየን 856 ሺህ 60 ብር እንዲሁም 101 ቤቶች፣ 19 መስሪያ ቦታ ሼዶች እና 178 ነጥብ 62 ሄክታር መሬት የሕዝብ መብትና ጥቅም ማስከበር መቻሉን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ክርክር በፍርድ ቤቶች የመርታት አቅም ወደ 94 ነጥብ 7 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ 92 ነጥብ 7 በመቶ በማሳካት አፈፃፀሙም 98 በመቶ መድረሱን አመላክተዋል፡፡

5 ሺህ 416 የግል አቤቱታ እና 981 የደንብ መተላለፍ በጥቅል 6 ሺህ 397 የወንጀል መዛግብት በመመርመር የማጥራት ሥራ መሰራቱን ገልጸው÷ ምርመራቸው ከተጠናቀቀባቸው የግል አቤቱታ ወንጀል መዝገቦች ውስጥ 4 ሺህ 639 መዛግብት በእርቅ እልባት አግኝቷል ብለዋል።

በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶ ውሳኔ ካገኘባቸው 1 ሺህ 314 የወንጀል መዛግብት በ1 ሺህ 307 መዝገቦች ላይ ማስቀጣት መቻሉንና 7 መዛግብት በነፃ መዘጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም 6 የነባር ሕጎች ማሻሻያ እና 30 አዳዲስ ሕጎች የማርቀቅ ተግባር ባለፉት ስድስት ወራት መከናወኑንም አቶ ተክሌ አስረድተዋል።

በአድማሱ አራጋው

Exit mobile version