Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሶማሌ ክልል የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን የማሳደግ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ በክልሉ የሕክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማሳደግ ጤናማና አምራች ዜጋ የማፍራት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ።

ካራማራ አጠቃላይ ሆስፒታል ያስገነባው የእናቶች እና ህጻናት ማዕከል ተመርቆ አገልግሎት ጀምሯል።

አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት÷ ማዕከሉ ፈጣንና ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል።

የክልሉ መንግሥት ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት የሚያስችሉ የጤና አገልግሎቶችን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በአሁን ወቅት ፈጣንና ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም ለእናቶች እና ህጻናት ጤና ትኩረት በመስጠት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የሰው ኃይል እና ግብዓት ማሟላት ላይ ትኩረት መደረጉን አንስተዋል።

የካራማራ አጠቃላይ ሆስፒታል ያስገነባው የእናቶች እና ህጻናት ማዕከል የህክምና አገልግሎት አሰጣጡን እንደሚያሻሽል ጠቅሰዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሴ አህመድ በበኩላቸው÷ በ2018 በጀት ዓመት በጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎትን ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ የተመረቀው ማዕከል 100 አልጋዎች እንዳሉት መግለፃቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

Exit mobile version