አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የህብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሐፊ ኡሎፍ ስኩጊ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ምክትል ዋና ፀሐፊውን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው በሁለቱ ወገኖች ትብብርና የቀጣናው ሰላምና ደኀንነት ዙሪያ አነጋግረዋል።
የአውሮፓ ሕብረትና አባል ሀገራቱ የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋሮች መሆናቸውን ገልጸው፥ በጋራ እሴቶችና ተስፋዎች ላይ የተመሰረተ ወሳኝ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ውህደት በቁርጠኝነት የምታደርገውን ጥረት ያብራሩት ሚኒስትሩ÷ እንቅስቃሴው ከአውሮፓ ህብረት የ2027 ግሎባል ጌትዌይ ኢኒሼቲቭ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ገልጸዋል።
እየተከናወነ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የበለጠ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ምክትል ዋና ፀሐፊው በበኩላቸው ÷ ህብረቱ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የሚያደርገውን ድጋፍና ስትራቴጂያዊ አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ የኮፕ 32 አስተናጋጅ ሆና በመመረጧ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ የኢትዮጵያን የልማት ውጥኖች ከግብ ለማድረስ ህብረቱ አስፈላጊውን ትብብር ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
በውይይታቸው ሁለቱም ወገኖች በጋራ ጥቅም ላይ በሚያተኩሩ ጉዳዮች አብረው ለመስራት መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

