Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደጉ ካሉ ሀገራት አንዷ እንድትሆን አስችሏታል – አቶ አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደጉ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን አስችሏታል አሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ፡፡
‎‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ቁልፍ የመንግሥት ፋይናንስና ሌሎች የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማትን ያሰባሰበው የኢትዮጵያ የፋይናንስ እመርታ ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ በኮንፈረንሱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ከሰባት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ስብራት ውስጥ ገብቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ከለውጡ በፊት የነበረው የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባት የእዳ ጫና፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የገበያ አለመረጋጋት እንዲከሰት ‎ምክንያት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት እነዚህን ስብራቶች ለመለወጥ በወሰዳቸው ርምጃዎች አሁን ላይ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል።
የመጀመሪያውና ሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ጠንካራና አዳዲስ ተቋማት እንዲፈጠሩ ማስቻላቸውን ገልጸው÷ ይህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ በፍጥነት እያደጉ ካሉ ሀገራት መካከል እንድትሆን አስችሏታል ነው ያሉት።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው የመንግስት ገቢን ለማሳደግ የሚያግዙ ጠንካራ፣ አዳዲስ እና ቀልጣፋ ስትራቴጂዎች እንዲነደፉ ማድረጉን እንዲሁም የመንግስት ገቢና የውጭ ፍሰት በአምስት እጥፍ እንዲያድግ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የመንግስት ጠቅላላ ገቢ በ2010 ዓ.ም ከነበረበት ዛሬ ላይ 446 በመቶ መጨመሩንና ከውጭ ሃብት ፍሰትም ባለፉት ሰባት ዓመታት በአጠቃላይ 25 ቢሊየን ዶላር ማግኘት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በድህነት ተኮር ዘርፎች የዋለው በጀት በ2010 ከነበረበት በአራት እጥፍ ማደጉን ጠቁመው፥የበጀት ጉድለትን በተመለከተ በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 2 ነጥብ 5 በመቶ በ2017 ወደ 0 ነጥብ 9 በመቶ መቀነስ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
Exit mobile version