አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከጥምቀት በዓል አከባባር ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከበዓሉ አከባባር ጋር ተያይዞ ቦታዎች ለማስዋብ በሚደረገው ጥረት የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች እና ጎብኚዎች የሚሳተፉበትን የጥምቀት በዓል በድምቀት ለማክበር አደባባዮች እና ጎዳናዎችን የማስዋብ ሥራ እንደሚከናወን ጠቅሷል።
የማስዋብ ሥራው ከሚከናወንባቸው ግብዓቶች መካከል የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች እንደሚገኙበት ገልጾ፤ የማስዋብ ሥራዎች ሲከናወኑ ከኤሌክትሪክ ምሰሶዎች፣ ትራንስፎርመሮች እና ማስተላለፊያ መስመሮች በበቂ ርቀት መከናወኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝቧል።
የእሳት አደጋ እንዳይከሰት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል፡፡
በበዓላት ወቅት በኤሌክትሪክ ማሰራጫ ምሰሶዎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ በተሽከርካሪዎች የመገጨት አደጋ የሚደርስበት አጋጣሚ እንደሚከሰት አስታውሶ፤ አሽከርካሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
በማንኛውም ወቅት የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ በተቻለ መጠን ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት መራቅ አደጋን ለመከላከልና ለመቀነስ የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝቧል።
ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት የበኩልን ትብብር እንዲያደርግ የጠየቀው ተቋሙ፤ ከኤሌክትሪክ ጋር በተገናኘ አደጋ ካጋጠመ ወይም ለሌላ መረጃ በ905/904 ላይ በመደወል ማሳወቅና መጠየቅ እንደሚቻል ገልጿል።
ለአደጋ መንስኤ የሚሆኑ መሰረተ ልማቶችን አስቀድሞ በመለየት የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት ምሰሶ የመቀየር፣ ያልተሸፈኑ መስመሮች በሽፍን ገመድ የመተካትና መሰረተ ልማቱን መልሶ የመንገባትና የማሻሻል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክቷል።
ለበዓሉ የኃይል መቆራረጥን በመቀነስ አስተማማኝና ቀልጣፋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማቅረብ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መከናወኑን ተቋሙ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
በመላኩ ገድፍ

