አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተቀናጀ አመራርና የሕዝብ ንቅናቄ ካለ የማይታለፍ ተራራ፣ የማይፈታ የልማት ጥያቄ የለም አሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲ ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ መጠናቀቁን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት÷ መድረኩ ካለፉት ስኬቶቻችን ልምድ የተቀሰመበት፣ ድክመቶች በብልፅግና እሳቤ የተመዘነበት መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ቀጣይ ፓርቲያችንን ይበልጥ የሚያጠናክሩ እና የሕዝባችንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በቁርጠኝነት ለመፈፀም አቅጣጫ ያስቀመጥንበት ነበር ብለዋል።
ከመድረኩ በኋላ በከምባታ ዞን የብልፅግና ፓርቲ ሰው ተኮር ልማት ስራዎች መመልከታቸውን ገልጸው÷ የከምባታ ሕዝብ የሚታወቅበት የታታሪነት፣ ትምህርትና ሥራ ወዳድነት እንዲሁም የእንግዳ ተቀባይነት እሴት ለዛሬው ስኬታችን ትልቅ መሠረት መሆኑን ዳግም አረጋግጠናል ነው ያሉት።
ሀምበሪቾ 777 ላይ የተመለከትነው እጅግ ማራኪ ተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ፀጋን ወደ ልማትና ቱሪዝም የመቀየር ጥበብን ጭምር ነው ብለዋል።
ይህም የሕብረተሰቡን ተሳትፎና የመንግሥትን አመራር በማቀናጀት ትልልቅ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የተቀናጀ አመራርና የሕዝብ ንቅናቄ ካለ የማይታለፍ ተራራና የማይፈታ የልማት ጥያቄ እንደሌለ በአካባቢው ያየናቸው የልማት ሥራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች የሚያረጋግጡት አንድ ትልቅ እውነት እንደሆነም አመልክተዋል።
የከምባታ ዞን አመራሮችና መላው የዞኑ ሕዝብና አመራር ላደረጉት ደማቅ አቀባበልና እያሳዩ ለሚገኙት የልማት ቁርጠኝነትም ምስጋና አቅርበዋል።

