አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በቴክኖሎጂ የታገዙ የግብርና ምርምሮችን ለማስፋት እየሰራ ነው አሉ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር)።
ኢንስቲትዩቱ የምግብና የተመጣጠነ ምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብርና ስርዓትን ማጠናከር ላይ ያተኮረ ሲምፖዚየም አካሂዷል።
ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢንስቲትዩቱ የሚያከናውናቸውን የግብርና ምርምር ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የቴክኖሎጂ አቅሙን ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።
በተለይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ በማዋል የምርምር ስራዎችን ይበልጥ የተቀላጠፈ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።
እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ብሎም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ በሚገኙ የልማት ስራዎች ተቋሙ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር በመለየት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
ለአብነትም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በበጋ መስኖ የስንዴ ልማት መርሐ ግብር የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመለየትና የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ምርምር በማድረግ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል።
ይህንን በማጠናከር ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች በመስኖ የሚከናወነውን የስንዴ ልማት ለማስፋት ከሰብል ዝርያዎች በተጨማሪ የአፈር ምርምር ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።
ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብርናን ማስፋፋትና የተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንደሚገባ በሲምፖዚየሙ ላይ ተመላክቷል።
በኃይለማርያም ተገኝ

