አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተሰራውና ከመተሐራ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው ቤኑና መንደር ሩቅ ሆነው እንዲሁም በምስል ለሚመለከቱት ግሩም የሆነውን ድንቅ የአረንጓዴ ውበት ይዟል።
ወደ ቤኑና መንደር ደርሰው ውስጥ መግባት ሲጀምሩ በመንገዱ ግራ እና ቀኝ እንደ ወታደር በተጠንቀቅ የቆሙት ዛፎች የሚለግሱት ጥላ እና ቀዝቃዛ አየር የመጡበትን ሞቃታማ መንገድ በማስረሳት መንፈስን ያድሳሉ።
ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ከሁሉም ቀድሞ የተመልካችን ቀልብ የሚስበው የበሰቃ ሐይቅ ከነፋሱ ጋር እየተወዛወዘ እንኳን ደህና መጣችሁ የሚል ይመስላል።
ረጋ ያሉ ሞገዶችን በመፍጠር ለጥ ብሎ በሚታየው ሐይቁ ዙሪያ የተለያዩ የወፍ ዝርያዎች የሚኖሩበት ሲሆን÷ በአካባቢው ምቹ የሆነ ሥነምሕዳር በመፍጠር ጎብኚዎች ቆም ብለው እንዲመለከቱ ያስገድዳል።
የሐይቁን ዙሪያ በመከተል የተገነባው ይህ መንደር እጅግ ሰፊ እና ከአንዱ ጫፍ ተነስቶ ሌላኛው ጋር ለመድረስ ረጅሚ ደቂቃዎችን ሊወስድ ይችላል።
ከመዝናኛ ስፍራነት ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን በውስጡ አቅፎ የያዘው ቤኑና÷ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው ባሕላዊ የኪነ ሕንጻ ጥበብን ከዘመናዊ ግንባታ ጋር ያዋሄዱ ህንጻዎች ሲታዩ ለዓይን ይማርካሉ።
በለምለም ሳር በተከበበው መንገድ ላይ ሲራመዱ በየቅርብ ርቀቱ የአካባቢውን ባህል የሚያንጸባርቁ በድንቅ ጥበብ የተሰሩ ቅርጻቅርጾችን መመልከት በራሱ ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነው።
በውስጡ ውብ ሆነው የተገነቡ ባሕላዊ እና ዘመናዊ ሬስቶራንቶችና ካፍቴሪያዎች የሚገኙ ሲሆን÷ እጅግ ዘመናዊ መኝታ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች እና ሲኒማ ቤት በውስጡ አቅፎ ከያዛቸው ጥቂቶቹ ናቸው።
በቤኑና መንደር እጅግ ከሚያስደንቁ ስራዎች መካከል ከአንድ ጫፍ ሆኖ ሌላኛውን ጫፍ ለመመልከት የሚያዳግት ትልቅ የእርሻ ቦታ ያለው ሲሆን÷ በውስጡ ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎችን ያመርታል።
እንዲሁም በመንደሩ የተደራጁ የእንስሳት ማራቢያ ስፍራ ያለ ሲሆን÷ በውስጡ ላሞች፣ ግመሎች፣ ፍየሎች እና ዶሮዎችን ጨምሮ የተለያዩ እንስሳት በተሰራላቸው መኖሪያ ግቢዎች ውስጥ ይኖራሉ።
መንደሩ በውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ለተሰማሩ ሰራተኞች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለአካባቢው ከፍተኛ የሆነ የቱሪዝም መነቃቃት እንዲፈጠር ትልቅ እድል የፈጠረ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስጀመሩት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተገነባው ቤኑና መንደር÷ የተተወ አካባቢን በማልማትና ወደ ቱሪዝም ማዕከልነት በመለወጥ የኢትዮጵያን የመልማትና የመበልጸግ አቅም የሚመሰክር ምልክት ሆኗል።
ቤኑና ራዕይን ይዞ በመስራት ምንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል የሚያሳይ ሲሆን÷ ከደረቅና ከተረሳ መሬት ውስጥ ያማረ የአትክልት ስፍራ፣ የቱሪስት መስህብ እንዲሁም ለነዋሪዎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።
በዮናስ ጌትነት

