አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።
በስርዓተ ቀብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የኪነ ጥበብ ቤተሰቦች፣ አድናቂዎቹ እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቹ ተገኝተዋል።
ባደረበት ህመም ጥር 8 ቀን 2018 ዓ.ም በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ በቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢነት፣ በፊልም ደራሲነትና አዘጋጅነት፣ በተዋናይነት እና በሌሎች የጥበብ ስራዎቹ በኪነ ጥበቡ ቤተሰብ ዘንድ ይታወቃል።
ሁለገቡ አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ለበርካታ ዓመታት በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የሚተላለፈውን የቤተሰብ ጨዋታ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን አገልግሏል።
አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ በፊልም እና በቴአትር ስራዎቹ እጅግ ተወዳጅ የነበረ ሲሆን፤ ሲቲ ቦይስ፣ ሳልነግራት፣ ያንቺው ሌባ፣ ኤፍቢአይ፣ ሚስተር ኤክስ፣ ቾምቤ እና ሌሎችም ድንቅ ብቃቱን ያሳየባቸው ፊልሞች ናቸው።
ፍሬሽ ማን ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀው የቴአትር ስራው ነው።
አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ባለትዳርና የ3 ልጆች አባት ነበር።

