አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ በጎዳና ላይ በጉሊት ንግድ ይተዳደሩ ለነበሩ እናቶች ዘመናዊ የንግድ ሼድ እና ግብዓት በዛሬው ዕለት አስረክበዋል።
ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በከተማችን በስፋት የተገበርነውን የኮሪደር ልማት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ የቀድሞውን የጉሊት ንግድ በማንሳት ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ የንግድ ሼድ ገንብተናል ብለዋል።
በጉሊት ንግድ የሚተዳደሩ እናቶች የምርት አቅርቦት ችግር እንዳይገጥማቸው ከላፍቶ ገበያ ማዕከል ጋር ዘላቂ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር መደረጉንም ጠቁመዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ጽዱ፣ ሰፊ የሚኪና ማቆሚያ፣ ካፍቴሪያ እና በቂ የንፅህና ቤቶች ተሟልቶ ከተገነባለት የገበያ ስፍራ እና ከእነዚህን ጠንካራ እናቶች ምርታቸውን በመሸመት እንዲያበረታቷቸው አሳስበዋል።
ልማታችን ሰው ተኮር ነው ስንል ይህ ተግባር አንዱ ማሳያ ነው ያሉት።
እነዚህ እናቶች ለረጅም ዓመታት ፀሐይና ብርድ እየተፈራረቀባቸዉ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው፣ ጤናቸው እየታወከም ቢሆን ለኑሮ ሲሉ በሜዳ ላይ ጉልት እየቸረቸሩ ልጆቻቸውን ያስተማሩና ቤተሰብ ያስተዳደሩ ብርቱ እናቶች ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም ዛሬ የሚገባቸውን ክብር አግኝተውና ተደስተው በማየታችን እኛም ደስ ብሎናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

