አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጥምቀት በዓል አከባበር የመዲናችን የቱሪስት መስህብ ሆኖ ይቀጥላል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
የጥምቀት በዓል በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ሀይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ እየተከበረ ይገኛል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕከት÷ ጥምቀት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የዳግም ልደትና የመገለጥ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ካለው ፍቅር የተነሳ ሰውን ሁሉ ለማዳን ከቅድስት ድንግል ማርያም በቤተልሔም ተወልዶ በዮርዳኖስ ባህር መጠመቁን መጽሀፍ ቅዱስ ያስረዳል ነው ያሉት፡፡
የጥምቀት በዓል ዋና ዓላማው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገውን በምሳሌነት በመከተል መኖር ነው ያሉት ከንተባዋ÷ በዓሉን ከጥላቻና ቂመኝነት ርቀን፣ የመራራቅ ግድግዳዎችን በማፍረስ በፍቅር ማክበር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርስነት ከተመዘገበ ስድስት ዓመት እንዳለፈው አስታውሰው፥ ከሀይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ባህላችንን፣ ቋንቋችንን እና ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለዓለም የምናሳይበት በዓል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባ በህብረ ብሔራዊነት ምሳሌ ጽዱ ሆና፣ አጊጣ እና ተውባ ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥታለች ያሉት ከንቲባዋ÷ በዚህም በርካታ ቱሪስቶች በበዓሉ እንዲገኙ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ይህንን ውጤት ለማስመዘገብ የከተማ አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር በትብብር ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፥ በዓሉ ስኬታማ እንዲሆን ትብብር ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የጥምቀት በዓል አከባበር በርካታ ቱሪስቶችን በመሳብ የመዲናዋ የቱሪዝም መስህብ ሆኖ ይቀጥላል ያሉት ከንቲባዋ፥ ሁላችንም በፍፁም ኢትዮጵያ ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት የሀገርን ገፅታ ለማስተዋወቅ ልንሰራ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

