አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ በልዩ መንፈሳዊ ስርዓት በድምቀት ከምታከብራቸው አበይት በዓላት አንዱ የጥምቀት በዓል ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰላሳ ዘመኑ በዮርዳኖስ ባሕር በዮሐንስ እጅ ተጠምቋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ የመጠመቁ ምክንያት ቅዱስ የሆነው እርሱ ሊቀደስ ሊከብር ሳይሆን የሰው ልጆች በጥምቀት የሚቀደሱበትንና ልጅነትን የሚያገኙበትን ውሃ ሊቀድስ መሆኑንም የእምነቱ አባቶች ያስረዳሉ።
ቤተክርስቲያኗም ይህንን መነሻ በማድረግ የጥምቀቱን ምስጢር በልዩ ልዩ ሁነቶች ገልጣ ታስተምራለች፥ ታከብራለች።
በዓሉ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበር ሲሆን፥ በዋዜማው ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ መጠመቁን አብነት በማድረግ ታቦታቱ ከማደሪያቸው ወጥተው ወደ ባህረ ጥምቀት ይሄዳሉ።
‘ከተራ’ በመባል የሚከበረው የበዓሉ ዋዜማ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱ ምሳሌ የሚገለጽበት እንደሆነ የቤተክርስቲያኗ ሊቃውንት ያስረዳሉ።
ሊቃውንቱ እንደሚሉት ጌታችንና መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁ በርካታ ምስጢራት የተገለጡበትና አስቀድሞ የተነገሩ ትንቢቶች የተፈጸሙበት ነው።
ዮርዳኖስ መነሻው አንድ ነው፥ ከዚያ በደሴት ወደ ሁለት ይከፈልና ተመልሶ ይገናኛል፡፡
ይህም የሰው ሁሉ ዘር አንድ (አዳም) ሆኖ ሳለ ሕዝብና አሕዛብ ተብሎ ተከፍሎ ከቆየ በኋላ በክርስቶስ ጥምቀት ዳግመኛ አንድ መሆኑን ለማጠየቅ በዮርዳኖስ መጠመቁን ታስተምራለች።
ሊቃውንት ጌታ በዮርዳኖስ የተጠመቀበት ምሥጢራዊ ምክንያት የሰው ልጆችን የዕዳ ደብዳቤ ሊያጠፋ ነው በማለት ይገልጻሉ።
ይህንን ሲያብራሩም፥ አዳምና ሔዋን ዕፀ በለስን በልተው ከተሳሳቱ በኋላ ዲያብሎስ መከራ ባጸናባቸው ጊዜ ስመ ግብርናችሁን ጽፋችሁ ከሰጣችሁኝ መከራችሁን አቀልላችኋለሁ ብሏቸዋል ይላሉ።
እነርሱም ይሁንብን በማለታቸው በሁለት እብነ ሩካብ ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱንም በሲኦል ጥሎት ስለነበር፥ ጌታ ሲጠመቅ እንደ ሰውነቱ ረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ የእዳ ደብዳቤያቸውን አጥፍቶላቸዋል በማለት ያስረዳሉ፡፡
ይህም ለጥምቀቱ ዮርዳኖስ የተመረጠበት ምክንያት መሆኑን ቤተክርስቲያኗ አመስጥራ ታስተምራለች።
መዝሙረኛው ዳዊት አስቀድሞ ስለ ዮርዳኖስ በትንቢት የተናገረው የተፈጸመበት መሆኑንም ነው የእምነቱ አባቶች የሚያብራሩት።
በቅዱስ መጽሐፍ እንደሰፈረው፥ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ “አንቺ ባሕር የሸሸሽ፣ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ ምን ሆናችኋል? እናንተም ተራሮች፣ እንደ ኮርማዎች፣ ኮረብቶችስ እንደ በጎች ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ? ከያዕቆብ አምላክ ፊት፣ ከእግዚአብሔር ፊት ምድር ተናወጠች” በማለት ተናግሯልና ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጥምቀት በዓልን ስታከበር የጌታን ወደ ዮርዳኖስ መሄድ አብነት በማድረግ ታቦታቱ ከማደሪያቸው ወጥተው በዝማሬ ታጅበው ወደ ባህረ ጥምቀት ይሄዳሉ።
ምዕመኑና መዘምራንም፥
“አንቺ ዮርዳኖስ ምንኛ ታደልሽ፣
የእግዚአብሔር መንፈስ ከላይ ወርዶልሽ
የዓለም መድሃኒት ተጠመቀብሽ” እያሉ በዝማሬ ታቦታቱን ያጅባሉ።
በኃይለማርያም ተገኝ

