አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኪው ኤስ የዓለም ዩኒቨርሲቲ ደረጃዎች መሰረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ደረጃ ይዟል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚያስመዘግቧቸው የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ውጤቶችን በመመዘን የዩኒቨርሲቲ ደረጃዎችን በሚያስቀምጠው QS World University Rankings አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ ዩኒቨርሲቲነት ደረጃን መያዝ ችሏል።
የደረጃ አሰጣጡ ዩኒቨርሲቲዎች ከሀገራቸው አልፈው በሌሎች ሀገራት ያላቸውን ተቀባይነት ከግምት ያስገባ ሲሆን÷ በዚህም ከምስራቅ አፍሪካ አራት ዩኒቨርሲቲዎች የቀጣናውን ተመራጭ ዩኒቨርሲቲነት ደረጃ ይዘዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ በተከታታይ ባስመዘገቡት የማስተማር፣ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ብቻም ሳይሆን በፈጠራ እና በቀጣናው ልማት ላይ ያበረከቱት አስተዋፅኦ በመመዘኛነት ቀርቧል።
በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ቀዳሚ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሆነው እና ዘንድሮ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት እያከበረ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀዳሚነት ተመርጧል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በመከተል የዩጋንዳው ማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ÷ የኬንያው ናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ እንዲሁም የሱዳኑ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካርቱም አራተኛ ደረጃ መያዛቸው ተመላክቷል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሂውማኒቲስ፣ ሶሻል ሳይንስ፣ ኢንጂነሪንግ እና የጤና ሳይንስ ጠንካራ ስራዎችን የሰራ ሲሆን÷ በርካታ የምርምር ተቋማቱም ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ ዘግቧል።
ዩኒቨርሲቲው ባከናወናቸው ስራም ከኢትዮጵያ ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ትልቅ ሚና የሚጫወት ቁልፍ ተቋም እንደሆነ ዘገባው አመላክቷል።

