አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጥምቀት በዓል የእግዚአብሔር የማዳን ሚስጥር በተጨባጭና በሚታይ ሁኔታ የተገለጠበት ነው አሉ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከተ የቦሌ ቡልቡላ ልበ ማርያም ቤተክርስቲያን ቆሞስ አባ አስፋው ጌታቸው።
የጥምቀት በዓል በዛሬው ዕለት በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ተከብሯል።
ቆሞስ አባ አስፋው ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት ውስጥ ማዕከላዊ ቦታ ያለው ነው።
በዓሉ መገለጥ (አስተርእዮ)፣ መዳን እና ተልዕኮ የሚገናኙበት እንደሆነ ገልጸው÷ የእግዚአብሔር የማዳን ሚስጥር በተጨባጭና በሚታይ ሁኔታ የተገለጠበት ቅጽበት ነው ብለዋል።
የጥምቀት በዓል የእግዚአብሔርን ሚስጥር፣ የመዳንን ባህሪ እና መንፈሳዊ ትርጉም የሚገልጥ በዓል እንደሆነም አብራርተዋል።
ጥምቀት በዮርዳኖስ ወንዝ ሰማይ የተከፈተበት፣ የአብ ድምፅ የተሰማበት፣ ወልድ የተጠመቀበት፣ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል በግልጽ የወረደበት የሥላሴን ሕይወት ለሰው ልጅ የገለጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክርስቲያናዊ ጥምቀት ምዕመናን በዚህ የተቀደሰ እውነታ ሲሳተፉ ውሃው ተራ ቁስ መሆኑ ቀርቶ መንፈሳዊ የመንጻት፣ ዳግም የመወለድና ከእግዚአብሔር ጋር የመዋሐጃ መንገድ ይሆናልም ነው ያሉት።
በጥምቀት አማካኝነት ምዕመናን ከሐጢአት ይነጻሉ፣ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነው ዳግም ይወለዳሉ እንዲሁም የክርስቶስ አካል በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይካተታሉ ብለዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ ካሳየው ትሕትና የሃይማኖቱ ተከታዮች ብዙ ትምህርቶችን እንደሚማሩበት ገልጸው÷ ለእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዮናስ ጌትነት

