Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዞታው ባሻገር የአንድነትና የመተሳሰብ መገለጫ ነው – ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዞታው ባሻገር የአንድነትና የመተሳሰብ መገለጫ ነው አሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ።

የጥምቀት በዓል የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባደሮችና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በጃን ሜዳ በድምቀት ተከብሯል።

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተወካያቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በኩል ባስተላለፉት መልዕክት÷ ለሀገራዊ አንድነትና ማህበራዊ ትስስር መጎልበት በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሰላምን ማጽናትና አብሮነትን ማጠናከር የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑን የጠቀሱት አቡነ ዲዮስቆሮስ÷ የሀገርን ልማት ለማረጋገጥ በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውንና አባቶች ጠብቀው ያቆዩትን የጥምቀት በዓል የአሁኑ ትውልድም የማጠናከርና የመጠበቅ አደራ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የጥምቀት በዓል የእምነት መግለጫ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የመፈቃቀርና የጨዋነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ በመጠመቅ የሰውን ልጅ ከሐጢያት እንዳነጻ ሁሉ ምዕመናንም የጥምቀቱን መንፈሳዊ ዓላማ በመረዳት በእለት ተእለት ሕይወታቸው ሊተረጉሙት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ቤተክርስቲያኗ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ የድርሻዋን መወጣቷንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version