Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በቀጣናው ለአየር መንገደኞች አያያዝ መሻሻልና መረጋገጥ ቁርጠኛ የሆነችው ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዮሐንስ አበራ ኢትዮጵያ በቀጣናው ለአየር መንገደኞች አያያዝ ደህንነት መሻሻል እና መረጋገጥ ቁርጠኛ ናት አሉ ።

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የአቪዬሽን ልዑካን የተገኙበት የአየር ትራንስፖርት ደንበኞች አያያዝን የተመለከተ ዐውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ለሶስት ቀናት የሚቆየው ዐውደ ጥናት በአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ለመንገደኞች ደህንነት ወጥ የሆነ ትኩረት ለመስጠት እንደሚረዳ ተመላክቷል።

አቶ ዮሐንስ አበራ በመድረኩ እንዳሉት፤ የመንገደኞች ደህንነት የሚረጋገጠው በመንግሥታት፣ በአየር መንገዶች፣ በተቆጣጣሪዎች እንዲሁም በአገልግሎት ሰጪዎች ነው።

የተናጠል ጥረቶችን ተቋማዊ በሆነ መልኩ በጋራ በመተግበር የመንገደኞችን ደህንነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የመንገደኞች አያያዝ ሁኔታ፣ እንግልት እንዲሁም ንብረቶቻቸውን ከመጠበቅና ለአላስፈላጊ ወጪ የመዳረጋቸው ጉዳይ የአየር እንቅስቃሴ ውስጥ ወቅታዊና አንገብጋቢ ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህንንም ለመቅረፍ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ አመልክተው፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ለአየር መንገደኞች አያያዝ ደህንነት መሻሻል እና መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኛ አቋም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 አንድ ወጥ የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ለመፍጠር ዓላማ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

በሰለሞን በየነ

Exit mobile version