Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጥምቀት በዓል …

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስ ተብሎ የተመዘገበው የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ካስቆጠሩ በርካታ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ ነው።

ጥምቀት የሚለው ቃል “አጥመቀ” ወይም “ነከረ” ከሚለው የግእዝ ሥርወ ቃል የተገኘ ሲሆን፥ ትርጉሙም “መጠመቅ ፣ መነከር፣ መደፈቅ፣ ውኃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ ማለት ነው” ስትል ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች።

ምስጢራዊና ሃይማኖታዊ ትርጉሙ ደግሞ፥ “የአብ የወልድ የመንፍስ ቅዱስ ልጅ መሆን ማለት ነው” ሲሉ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድርሳናት ይግልጻሉ።

በዓሉ በቤተክርስቲያኗ ተከታዮች ዘንድ ከዋዜማው ጥር 10 ጀምሮ እስከ ጥር 11 የሚከበር ሲሆን፥ ጥር 12 ደግሞ የቃና ዘገሊላ በዓል እንዲሁ በድምቀት ይከበራል።

“ገሀድ” በመባል የሚታወቀው ጥር 10 ቀን የጾም እለት ነው። የ“ገሀድ” ትርጉሙም መገለጥ ማለት ነው። ምክንያቱም “ወልድ የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ፣ በኋለኛው ዘመን ደግሞ ያለ አባት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆኖ ተዋሕዶ ስለተገለጠልን እና በ30 ዓመቱ በባሕረ ዮርዳኖስ በዮሐንስ ተጠምቆ ክብሩንና ጌትነቱን ስለገለጠልን ነው” ስትል ቤተክርስቲያን ታስተምራለች።

እንደ ቤተክርስትያን አስተምህሮ፥ ጌታ የተጠመቀው በ5 ሺህ 530 ዓ.ዓ በዘመነ ሉቃስ በእለተ ማክሰኞ ጥር 10 ለ11 አጥቢያ ከሌሊቱ በ10 ኛው ሰዓት በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር በ30 ዓመት ከ13 ቀኑ ነው።

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዘመኑ የተጠመቀው የሰው ልጆች ሁሉ አባት የሆነው አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ በ40 ቀኑ አግኝቶ በኋላ ያጣትን ልጅነት ለማስመለስ ነው ነው።

እርሱ አምላክ ሲሆን በዮሐንስ እጅ መጠመቁ ደግሞ ትህትናውን ለመግለጥ መሆኑን ቅዱሳን መጽሐፍት ይገልፃሉ።

በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት ከኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ዜማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን ታቦታት ጠዋት ከመምበረ ክብራቸው በመነሣት ወደ ወንዝ ወርደው ማታ ወደ መንበረ ክብራቸው ይመለሱ ነበር።

ይህ ሥርዓት እስከ ዛጒዌ ሥርወ መንግሥት ቀጥሏል። የሰማያዊ መቅደስን አምሳል በምድር በመሥራት በኪነ ሕንፃ ጥበቡ የከበረ ጻድቅ ቅዱስ የበዓሉ አከባበር በኢትዮጵያ ካህንና ንጉሥ የሆነው ቅዱስ ላሊበላ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ለየብቻው በሚቅርባቸው ቦታ ሲፈጽሙት የነበረውን ክብረ በዓል አስቀርቶ በአንድ ቦታ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአንድ ላይ በመሆን በአንድ ጥምቀተ ባሕር እንዲያከብሩ ትእዛዝ አስተላልፎ እንዲከበር አድርጓል።

በዚህም ምክንያት በዓሉ በይበልጥ የተለየና የደመቀ ሥርዓት እንዲኖረው ሆነ። በተያያዘም ጻድቁንና ቅዱሱን ባሕታዊ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን በአክሱም፣ በላስታ፣ በሸንኮራ፣ በአንኮበር፣ በመቐለና በመርጡለ ማርያም እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን እንዲባርኩ ማድረጋቸው ድርሳናት ይገልፃሉ።

በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት በ13 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይህ ሥርዓት ተጠናክሮና ተስፋፍቶ እንዲቀጥል በዐዋጅ አስተላልፈዋል። ሕዝቡም በነቂስ ወጥቶ ያከብር ነበር።

የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ፣ እየሰፋ ብሔራዊነትን እየያዘ እንደመጣ ይገለፃል። በዘመነ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ደግሞ በአንድ ቀን ሄዶ የሚመለሰው ሥርዓት ቀርቶ ጥር 10 ቀን ታቦቱ በኪደተ እግር ወርደው ውሆችን እንዲባርኩ በዚያም እንዲያድሩ በሄዱበትም እንዳይመለሱ (ሲሄዱ የባረኩትን ያህል በሌላ ቦታ ያለውን ሲመለሱ እንዲባርኩ የሃይማኖት ጽናት ብቻ ሳይሆን የወንጌል መንግሥት መስፋፋትን እየሰበኩ እንዲመለሱ) በዐዋጅ ወሰኑ።

ምእመናንም በሆታ፣ በእልልታ፣ በይባቤ በማክበር በቦታው በማደር ሥርዓቱን ይፈፅማሉ፤ ሊቃውንቱንም ለበዓሉ የሚገባውን ቃለ እግዚአብሔር በማድረስ ያድራሉ።

የሚዘመረው መዝሙር፣ የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔርም በጥምቀት የምናገኘውን ጸጋና በረከት የሚያመሠጥር ነው። የሚከናወነውን ሥርዓትም ሃይማኖታዊ ታሪክና ምሳሌ የሚጠይቅ ነው።

ይኸውም “ታቦቱ የጌታችን፣ ታቦቱን የሚሸከመው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ፣ ጥምቀተ ባሕሩ የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ታቦቱን አጅበው የሚሄዱ እና በዓሉን የሚያከብሩ ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩ ሰዎች ምሳሌ ናቸው።

ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ ጥምቀተ ባሕሩ መውረዳቸው ደግሞ፥ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ በባሕረ ዮርዳኖስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱን ያጠይቃል” ይላል የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ።

ዐዋጅ ነጋሪ በሆነው ቅዱስ ዮሐንስ የሚመሰለው የቤተ ክርስቲያን ደወል ሲደወል፥ ምእመናን ከልጅ እስከ ዐዋቂ በነቂስ ወጥተው በዐፀደ ቤተ ክርስቲያን ይሰባሰባሉ።

ታቦቱ በተለያዩ ኅብረ ቀለማት በተሸለሙ ልብሰ ተክህኖ የደመቁ ካህናትና የመፆር መስቀል ባነገቡ ዲያቆናት ታጅበው፣ ከቤተ መቅደስ ተነሥተው ወደ ጥምቀተ ባሕሩ ይሄዳል። ካህናቱም ጌታ ለመጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ መውረዱን በዝማሬያቸው ይገልጻሉ።

በገጠር ላሉት አብያተክርስቲያናት ታቦታቱ በወንዝ ዳር እንዲሁም በከተማ ደግሞ ለከተራ በተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ ማረፊያዎቸ እንዲያርፉ ይደረጋል።

ቀድመው በጥምቀተ ባሕሩ የተገኙ ምእመናን በእልልታ እና በስግደት ይቀበላሉ። መዘምራን ዝማሬ አቅርበው፣ ቃለ ቡራኬ ተሰጥቶ፣ ታቦታቱ በተዘጋጀላቸው ማደሪያ በመንበረ ክብራቸው ያርፋሉ።

ካህናቱም ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ ማኅሌት ሲያደርሱ ያድራሉ። ከምእመናን ወገን የበረታ በማኅሌት ያልቻለ በታቦታቱ ዙሪያ ድንኳን ከትመው ያድራሉ።

የዕለቱ ቅዳሴ ተቀድሶ ሲነጋ ካህናቱ ባሕረ ጥምቀቱን ከበው መጽሐፈ ጥምቀት ይነበባል። የዕለቱ ቃለ እግዚአብሔር ደርሶ ሲያበቃ ጥምቀተ ባሕሩ የሚገኝበት ቦታ መንበረ ፓትርያርክ ከሆነ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ የመንበረ ጵጵስና ቦታ ከሆነ ሊቀ ጳጳሱ ይህ ካልሆነ ደግሞ ቆሞስ አልያም በቦታው በክብርና በማዕረግ ከፍያለ ካህን ወይም ገባሬ ሠናይ ቄስ ባሕረ ጥምቀቱን ይባርካል።

አራት የሚበሩ ጧፎች የታሰረበት መስቀል ወደ ባሕሩ ይለቀቃል፤ ይህም ጌታችን ሲጠመቅ ብርሃን የመውረዱ ምሳሌ ነው።

ጸሎተ አኮቴት ደርሶ፣ ሥርዓተ ቡራኬ ከተፈፀመ በኋላ ሕዝቡ በረከት ለመቀበል ጸበሉን እየተሻሙ ይረጫሉ። በግፊያው ውስጥ ጉጉት አለ፤ በሽሚያ ውስጥ ፍቅር አለ። ረገጥኸኝ ብሎ፣ ተገፋሁ ብሎ ቅር የሚለው ሰው የለም፤ ሁሉም የሚረጨውን ጸበል ከሰውነቱ ጋር ለማገናኘት ይጓጓል።

የጸበሉን ፍንጣቂ ካገኘ ፍጹም በረከትና ሙሉ ጸጋ እንዳገኘ አምኖ ቦታውን ለሌላ ወገኑ ይለቃል። ምእመናን ቡራኬ ካገኙ በኋላ ታቦታቱ ካደሩበት ወጥተው በተዘጋጀላቸው ቦታ ይቆማሉ።

መዘምራንም ‹‹ኀዲጎ ተሰአ ወተስአተ ነገደ ቆመ ማእከለ ባሕር ገብአ ወወፅአ በሰላም፤ ዘጠና ዘጠኙን የመላእክት ነገድ ትቶ በባሕር መካከል ቆመ›› እያሉ ይዘምራሉ።

ከዚያም ቡራኬ ተሰጥቶ መንቀሳቀስ ይጀመራል፤ በዚህ እለት ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ”ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ” ትርጉሙም “ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ” በሚለው ያሬዳዊ ዝማሬ እና ለበዓሉ በተዘጋጁ ሌሎች የቤተክርስቲያን መዝሙሮችም በዓሉን ሲያደምቁት ይውላሉ።

እልልታ መዝሙሩ፣ ሽብሸባው ውዳሴው፣ ምስጋና ጸሎቱ ይደምቃል። ሕዝቡ በአንድነት እግዚአብሔርን በማመስገን ታቦታቱን አጅቦ ጉዞው ይቀጥላል።

ካህናቱ ወረቡን ሲያሳምሩ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን የመለያ ልብሳቸውን ለብሰው ሲዘምሩ፣ ጎበዛዝቱም በእልልታ፣ በሆታ ሲያመሰግኑ፣ እናቶች ትሕትናና ፍቅር በተሞላበት ምስጋና በታቦቱ ፊት ሲሰግዱና ሲማልዱ ሁሉም በየድርሻው በክብር አጅቦ ያወጣውን ታቦት በክብር ይመልሳል።

የጥምቀት በዓል በባህላዊ አለባበስ በደመቀ ሁኔታ የሚከበር መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። ምእመናን ማህበራዊ መስተጋብራቸውን የሚያጠናክሩበት ከማህበረሰቡ ባህል ጋር እጅግ የተጣመሩ መሆናቸውን የሚያሳዩበትም ነው።

በበዓሉ ሰሞን ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚደርስ የንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት ሂደት በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው።

ቱሪዝም ለማነቃቃትና ከሚገኘው ገቢ አካባቢዎቹን ተጠቃሚ ለማድረግም ጠቀሜታው ጉልህ ነው።

በማሕበራዊ ትስስር ዘንድ ሲታይም፥ የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ወቅት በየቤቱ የመስተንግዶ ዝግጅት ተደርጎ ወዳጅ ዘመድ ተጠራርቶ አብሮ ይመገባል፤ ይገባበዛል፤ ጎረቤት ይጠያየቃል፤ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ይደረጋል።

በዓሉ በባህል አልባሳት በመድመቅ የሚከበር ሲሆን፤ የሀገር ገጽታን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ በኩል ጉልህ ድርሻ አለው።

የበርካታ ቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ የሚታወቅ የጥምቀት በዓል አከባበር ለማክበርና ስነስርዓቱን ለመመልከት በየዓመቱ በርካታ ጎብኝዎች፣ ዲፕሎማቶችና አምባሳደሮች ይታደማሉ፡፡

በደስታ ተካ

ይህም ጽሁፍ ለማደራጀት ነገረ ሃይማኖት (ዘኦርቶዶክስ ተዋኅዶ) እና ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት መጽሐፍትን እንዲሁም የተለያዩ ዌብሳይቶችን በዋቢነት ተጠቅመናል።

Exit mobile version