አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የ2018 በጀት ዓመት ክልላዊ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በኮንሶ ዞን ካራት ማዕከል ተገኝተው በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች ምርታማነትን ያሳድጋሉ።
ይህም የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትንና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ለተያዘው ራዕይ ስኬት ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።
የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ ምርታማነትን እንደሚያሳድግ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ከሀገር በቀል ተሞክሮዎች ጋር ማቀናጀት እንደሚገባ አስገንዝበው፤ ህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ብልጽግናን እውን ለማድረግ እና ደህንነቱ የተረጋገጥ ከባቢን ለትውልድ ለማሻገር በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በክልሉ በተከናወነ የተፋሰስ ልማት ስራ ከ164 ሺህ በላይ የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
በጌትነት ጃርሳ

