አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በኢትዮጵያ 309 መገናኛ ብዙኃን ተመዝገበውና ፈቃድ አግኝተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ አለ።
በህግ መሰረት የብሮድካስት አገልግሎት የፈቃድ ሁኔታን የሚወስነው፣ ፈቃድ የሚሰጠው፣ የሚያድሰው እና የሚያግደው ባለስልጣኑ፤ 254 በስርጭት ላይ እንዲሁም 55 መገናኛ ብዙኃን በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቋል።
በዚህም ፈቃድና ምዝገባ አግኝተዉ የሚንቀሳቀሱ 175 የብሮድካስት፣ 73 የበይነ መረብ፣ 20 የህትመት እና 35 የዉጭ መገናኛ ብዙኃን እንዳሉ ገልጿል።
እንዲሁም አምስት የክፍያ ኢንተርኔት ብሮድካስት እና አንድ ነፃ የኢንተርኔት ብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን በአጠቃላይ 309 መገናኛ ብዙኃን በባለሥልጣኑ ምዝገባ እና ፈቃድ አግኝተዉ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጿል።
ባለሥልጣኑ ባለፉት ስድስት ወራት ለ39 የመገናኛ ብዙኃን በፍቃድና ክትትል ዘርፍ የፍቃድ እና የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት አገልግሎት ሰጥቻለሁ ብሏል።
ባለፉት ዓመታት የዘርፉን እድገት ለማፋጠን በተተገበሩ የህግ እና የአሰራር ለዉጥ መገናኛ ብዙኃኑ በቁጥር፣ በዓይነት እንዲሁም በተደራሽነት እድገት እንዲያስመዝግቡ ማስቻሉንም አስገንዝቧል።
ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸውን እንዲጠበቅና መገኛ ብዙኃን በጎ ተፅዕኖ መፍጠር እንዲችሉ በኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል አማካኝነት ለጋዜጠኞች እየተደረገ ያለው ፕሮፌሽናል ስልጠና ለሚዲያው ምህዳር መሻሻል አንዱ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሷል።

