አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታል ግብርና በዘርፉ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የአቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍና የልማት ግቦችን በማሳካት ረገድ የበኩሉን ሚና ይጫወታል አሉ የዘርፉ ምሁራን።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የግብርና እሴት ሰንሰለት ሥራ አመራር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሀርቆ ሀላላ እና በመዳ ወላቦ ዩኒቨርሲቲ የሰብል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ጀማል አብዱልከሪም ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ዲጂታል ግብርና ለዘርፉ ምርታማነት ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል።
በዚሁም ዲጂታል ግብርና በጥቅሉ ሲተረጎም የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ለግብርና ስራዎች መጠቀም ነው በማለት ገልጸው÷ የተፈጥሮ ሃብት አያያዝ ችግሮችን እንደሚቀርፍ ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂዎቹ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የገበያ ተደራሽነትን በማስፋት፣ በአቅርቦት የእሴት ሰንሰለት ላይ መጠናከር፣ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት፣ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬነት ስራዎችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታን ይፋ ማድረጓ የሚደነቅና ወደፊት የማደግ እቅዷንም የሚያሳካ ነው ብለዋል።
ዘርፉ ካለው ሀገራዊ ፋይዳ አንፃር በፍጥነትና በልዩ ትኩረት ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት ምሁራን።
በአስጨናቂ ጉዱ

