አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የከተማዋ ንግድ ቢሮ፡፡
በቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የነዋሪዎችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የምርት አቅርቦትን ለማሳደግ ከባለድረሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሰንበት ገበያዎችና የገበያ ማዕከላትን ለማስፋፋት ትኩረት መደረጉን ጠቁመው ÷ በዚህም የምርት ተደራሽነትን ይበልጥ ማጠናከር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን በመቆጣጠር የገበያ መረጋጋት መፍጠር መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡
በተለይም በሕገ ወጥ መንገድ ምርት የሚያከማቹ፣ የሚሰውሩ እና ያለ አግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል፡፡
በዚህ መሰረትም በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት 6 ወራት ከ12 ሺህ በላይ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የተለያየ አስተዳደራዊ ርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል፡፡
ዘመኑን የዋጀ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ÷ ቢሮው በአሁኑ ወቅት 6 ዋና ዋና እንዲሁም 19 ንዑስ አገልግሎቶችን በኦንላይን እየሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በቀጣይ የተገኙ መልካም ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የአገልጋይነት መንፈስን በመላበስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
ሕብረተሰቡ በገበያ ሥርዓቱ ላይ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

