አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል የተደረሰውን ዘላቂ የሰላም ስምምነት ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት በዛሬው እለት ተፈርሟል።
በስምምነት ሥነ ሥርዓቱ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስን ጨምሮ የክልሉና የፌደራል መንግሥት እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮችና የአፋህድ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፥ በክልሉ የነበረው ግጭት ሕዝቡ ሊያገኝ የሚገባውን ልማት ያሳጣና ከፍተኛ ውድመትን ያስከተለ ነው፡፡
በዚህ በሰለጠነ ዘመን ከሰላም ይልቅ አፈ ሙዝ ይዞ መፋተግ ጊዜውን የማይመጥን እና በትውልድ ተወቃሽ የሚያደርግ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ዛሬ ላይ ሰላምን መርጠው ወደ ሰላም መንገድ የመጡት የአፋህድ አመራሮች ተገቢውንና ለትውልድ የሚበጅ ውሳኔ በመምረጣቸው ምስጋና አቅርበዋል።
ሌሎች ቀሪ ሀይሎችም የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ አቶ መሃመድ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፋህድ ከፍተኛ አመራር ፈንታው ሙሀባ በበኩላቸው÷ስምምነቱን እውን ለማድረግ ባለፉት ጊዜያት በአፍሪካ ህብረትና በኢጋድ አማካኝነት በህጋዊ መንገድ ስንወያይ ቆይተናል ብለዋል።
ስምምነቱ ያለፈውን የሚያጠናክር እና ህጋዊ በሆነ መልኩ የተፈፀመ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት።
በቤተልሔም መኳንንት

