አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፀጥታና ደህንነት ተቋማት 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየሰሩ ነው፡፡
ተቋማቱ 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ በተዘጋጀው የፀጥታ ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚህ ወቅት÷ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት በርካታ የፀጥታ ሥራዎችን በመስራት በተለያዩ ጊዜያት የተካሄዱ ታላላቅ ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ ማስቻላቸውን አውስተዋል።
39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የነበረውን ልምድ በመጠቀም በስኬት እንዲጠናቀቅ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የፀጥታና ደህንነት ተቋማት በሪፎርሙ የፈጠሩትን ከፍተኛ የሎጂስቲክስ፣ ቴክኖሎጂና የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅም በማስተባበር በተሟላ ዝግጅት በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
በዚህም የፀጥታና ደህንነት ተቋማት የኦፕሬሽን ቲም ተቋቁሞ በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያዋ እንዲሁም በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የጋራ ኦፕሬሽን እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ በሚያደርግ መልኩ በከፍተኛ ዲሲፕሊን እንግዶችን መቀበል እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
ቀድሞ በመዘጋጀትና የተጠናከረ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ጉባዔው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

