አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕድንና ነዳጅ ሃብቶችን በተገቢው መንገድ ማልማት ለዘላቂ ዕድገት ወሳኝ ነው አሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡
ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ጌትነት አሥራት (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የማዕድንና ነዳጅ ሃብቶችን በጥናትና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለይቶ ማወቅ ሀገሪቱ ለጀመረችው ዕድገት ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመጣመር የተጀመሩ ሥራዎች ላይ ምሁራንን ከማሳተፍ ባለፈ ዘርፉን በእውቀትና በምርምር የተደገፈ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
ዘርፉን በጥናትና በምርምር የታገዘ ለማድረግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር የተጀመሩ ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የማዕድን ጥናትና ምርምር መምህርና ተመራማሪ አሸናፊ ንጉሴ ናቸው፡፡
ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እየተገበረ ያለው መንግሥት ማዕድንን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የማዕድን ነዳጅ ሃብቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለሠላም፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለዘላቂ ልማት አስፈላጊ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ዘርፉ ለውጭ ምንዛሪና ለሀገር ውስጥ ገቢ ያለውን አስተዋጽኦ ለማጉላት የፖሊሲ፣ የአስተዳደር፣ የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ልማት ርምጃዎች በተቀናጀ መልኩ መፈጸም እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
የማዕድንና ነዳጅ ሀብቶች ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የጥሬ ዕቃ፣ የኃይልና የኬሚካል ግብዓቶችን በማቅረብ የኢኮኖሚ ለውጥን የሚያፋጥን ቁልፍ ሚና ሆኖ ያገለግላል ብለዋል፡፡
የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ከማዕድንና ነዳጅ ሀብቶች አንፃር ለማስፋፋት ግልጽ ፖሊሲ፣ የፋይናንስ ድጋፍ፣ የመንግሥት እና የግል ትብብር በተቀናጀ መልኩ በስፋት መተግበር እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።
ዘርፉ ለህገወጥ ተግባራት የተጋለጠ በመሆኑ ይህንን መከላከል እንደሚገባ ገልጸው÷ በፍትሃዊ መንገድ እና በአግባቡ ከተሰራ ሕዝቡን ከድህነት ለማውጣት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአስጨናቂ ጉዱ

