Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፈጣን እድገት ለአፍሪካ ሀገራት አብነት የሚሆን ነው – የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል እያስመዘገበ የሚገኘው ፈጣን እድገት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አብነት ይሆናል አሉ በኢትዮጵያ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ክብረ በዓልን በማስመልከት የተዘጋጀው የአቪዬሽን ኤክስፖ በዛሬው ዕለት ተከፍቷል።

“የወደፊቱን የአቪዬሽን አቅም በጋራ እንገንባ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀውን ኤክስፖ የጎበኙ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ በሚሆን አግባብ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የቦትስዋና ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል ሞታሲ ቼሌኒያኔ፥ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአቬዬሽን፣ ኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አስደማሚ የለውጥ ሒደት ላይ መሆኑን ከኤክስፖው መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በተለይ አየር ኃይሉ ጥገናን ጨምሮ በሌሎች ቁልፍ የዘርፉ ምህንድስና ስራዎች ራሱን ለመቻል እያከናወነ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፥ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከዚህ ልምድ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ የናሚቢያ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ማካንዚ ቺቤራ በበኩላቸው፥ ባለፉት ጊዜያትም ሆነ አሁን ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የራሱንና የአፍሪካን አቅም ለማሳደግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት በጋራ ከሰሩ ብዙ ርቀት መሄድ እንደሚችሉ የገለጹት ወታደራዊ አታሼው፥ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የወሰደውን ተነሳሽነት አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሀገር የሚወክል ታላቅ ተቋም ነው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የጋቦን ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል አርሲዴ ናቸው፡፡

ይህ የአየር ኃይሉ እድገት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ጥሩ ምሳሌ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version