Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአዲስ አበባ ከተማ የልማት ስኬቶች ለትውልድ የሚተላለፉ ናቸው – የአፋህድ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶች የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለትውልድ የሚተላለፉ ናቸው አሉ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) አመራር አባላት፡፡

የአፋሕድ ከፍተኛ አመራር አባላት በመዲናዋ የዓድዋ ድል መታሰቢያን፣ የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻና ሌሎች ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የውጭ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ማስረሻ ሰጤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ አዲስ አበባን ለማስዋብ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ለትውልድ የሚተላለፉ ናቸው፡፡

በኮሪደር ልማትና የመዝናኛ ስፍራዎች፣ በወንዝ ዳርቻና ቅርስ ጥበቃ ልማት የተመዘገቡ ስኬቶች መዲናዋን ዓለምአቀፍ ውብ ገፅታ በማጎናጸፍ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።

በተለይም በቅርስና ታሪካዊ ሥፍራ ጥበቃ የልማት ሥራ ላይ የተመዘገቡ ስኬቶች ቀጣዩን ትውልድ በሚቀርጽ የአሰራር ሥርዓት ተውበው የተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መዲናዋን በማስዋብ ሂደት ድጋፍና አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፌዴራል መንግስት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ባለድርሻ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በታሪካዊ ጠላቶች ፊት አውራሪነት በግጭት እንድትቆይ የተሸረበውን ሴራ በማጤን የሰላም አማራጭ እንደተቀበሉ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ላለፉት ዓመታት የተከሰተው ግጭት ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው በማስተጓጎልና የመሠረተ ልማት ግንባታን በማቋረጥ እንቅፋት መፍጠሩን አስታውሰዋል።

በስምምነቱ መሠረትም በጫካ የነበሩት ወደተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ ማዕከል በማሰባሰብ የህዝብ ሰላምና የልማት አካል ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

የመዲናዋ የልማት ስኬቶች ጉብኝት ኃላፊነት የወሰድንበት ነው ያሉም ሲሆን፥ በቀጣይ የአማራ ክልልን የመሰረተ ልማት ሥራ ለማስቀጠል እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የድርጅቱ ወታደራዊ አስተዳደር ኃላፊ እያሱ አባተ በበኩላቸው÷ በመዲናዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረጉ አስደናቂ የልማት ስኬቶች መመዝገባቸውን በጉብኝታቸው እንዳረጋገጡ አስረድተዋል።

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) አመራርና አባላት የሰላም አማራጭን መቀበል ለቀጣይ ሀገራዊ ልማትና ለህዝብ ተጠቃሚነት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የአፋሕድ የስልጠና መምሪያ ኃላፊ መልካሙ ጣሴ እንዳሉት፥ በአዲስ አበባ ከተማ የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል።

በተለይም በሰው ተኮር ልማት የተገነቡ ፕሮጀክቶች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version