Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለአየር ክልል ቁጥጥር መጠናከርና ለሀገር ሉዓላዊነት መጠበቅ ቁልፍ ሚና ያለው የባህር በር …

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ አየር ሀይል የአቪዬሽን ህክምና ባለሙያ ሰለሞን ጉርሙ (ዶ/ር) የባህር በር የአየር ክልል ቁጥጥርን በማጠናከር የሀገር ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ ያደርጋል አሉ፡፡

የኢፌዴሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።

ሰለሞን ጉርሙ (ዶ/ር) ክብረ በዓሉን አስመልክቶ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የኢትዮጵያ አየር ሀይል የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ሲያስከበር መቆየቱን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ሀይል እያደገ እና በዘመናዊ ትጥቆች ራሱን እያጠናከረ መምጣቱን ጠቅሰው÷ የተቋሙን እድገት የሚመጥኑ ወሳኝ እና አስፈላጊ ጉዳዮች እንዳሉ ተናግረዋል።

ከእነዚህ መካከል የአየር ክልል ቁጥጥር አቅምን ለማጠናከር ቁልፍ ሚና ያለው የባህር በር አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።

የአየር ክልልን ማጠናከር ለሀገር ሉዓላዊነት መጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በ1919 በወጣው የፓሪስ መርህ መሰረት አንድ ሀገር ባለው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ልክ የአየር ክልሉን እስከ 100 ኪሎ ሜትር ድረስ የመቆጣጠር መብት እንዳለው አብራርተዋል፡፡

የባህር በር ያላቸው ሀገራት ተጨማሪ የአየር ቁጥጥር አቅም ይኖራቸዋል ያሉት ባለሙያው፤ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ግን የባህር ዳርቻ ባላቸው ሀገራት ይሁንታ ብቻ የአየር ላይ እንቅስቃሴያቸው እንደሚወሰን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ከባህር በላይ ያለውን የአየር ክፍል በባለቤትነት መቆጣጠር እንደማይችሉ ገልጸው፤ ይህም ሉዓላዊነታቸው ላይ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ አዲስ የባህር በር እየፈለገች ሳይሆን የነበራትን መልሳ ለማግኘት እየጣረች ትገኛለች ያሉት ሰለሞን ጉርሙ (ዶ/ር)÷ ጥያቄው እንዲሳካ የጋራ ጥረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version