Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል የታጠቁ አካላት ወደ ሰላም መምጣታቸው ለዘላቂ ሰላምና ልማት ወሳኝ ነው – አቶ መሐመድ እድሪስ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የታጠቁ አካላት ወደ ሰላም መምጣታቸው ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ወሳኝ ነው አሉ የሰላም ሚኒሰትር መሐመድ እድሪስ፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለምአቀፍ ኮንፈረንስ “የሕግ የበላይነትና አማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች ለዘላቂ ሰላም እና ዕድገት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው፡፡
የሰላም ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያን ከግጭትና የድህነት አዙሪት አላቅቆ የበለፀገችና ለሌሎች ምሳሌ የምትሆን ሀገር ለመገንባት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
ከለውጡ ወዲህ የመልማትና የሁለንተናዊ ብልፅግና አጀንዳ ከፍ ብሎ መምጣቱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፥ በንግግር ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮችን በኃይል ለማስፈጸም የሚሞክሩ አካላት በህብረተሰቡ የሰላምና የመልማት ፍላጎት ላይ ችግር መፍጠራቸውን አንስተዋል።
በአማራ ክልል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትጥቅ ባነሱ አካላት የዘላቂ ሰላምና ልማት ሥራዎች መደናቀፋቸውን ገልጸው፥ መንግሥት ይህን በመገንዘብ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ባለው ፅኑ አቋም ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
የለውጡ መንግሥት ስለ ሰላም የዕይታና የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ዘላቂ ሰላምን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አካሄድን ቀዳሚ አማራጭ ማድረጉን ጠቅሰው፥ የማያግባቡ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትሕ ስርዓት ተዘርግቷል ነው ያሉት፡፡
በአማራ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የቆዩና መሳሳታቸው ለህዝብ መከራ እንደሆነ የተገነዘቡ ኃይሎች ወደ ሰላም መምጣታቸው ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል።
በመሆኑም የታሪክና የትውልድ ተጠያቂነትን ከሚያስከትል ጥፋት በመቆጠብ መንግሥት ለሠላም የሰጠውን ዕድል በመጠቀም ለዘላቂ ሰላም በጎ ሚና መጫወት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የዳበሩ የግጭት መፍቻና የፍትሕ ስርዓቶችን በአግባቡ መጠቀም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ በኮንፈረንሱ ላይ የተነሱት የህግ የበላይነት፣ አማራጭ ልዩነትን መፍቻ መንገዶች እንዲሁም የዘላቂ ሰላምና ልማት አጀንዳዎች አንገብጋቢና ወቅታዊ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
በለይኩን ዓለም
Exit mobile version