Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሃሳብ የሚሞግት ዜጋ መፈጠር አለበት – ያዕቆብ አርሳኖ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባኮረፈ ቁጥር የሚሸፍት ሳይሆን ልዩነት ሲኖረው መንግሥትን በሃሳብ የሚሞግት ዜጋ መፈጠር አለበት አሉ የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ያዕቆብ አርሳኖ (ፕ/ር)፡፡

በወቅቱ ያለው መንግሥት አስቀይሞኛል የሚል ኃይል ቢኖር እንኳን ለሌላ ጠላት እንደመቀጠር ዓይነት ተግባር ውስጥ መገኘት የለበትም ብለዋል፡፡

ያዕቆብ አርሳኖ (ፕ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ ለጠላት የመገበር ዓይነት አካሄድ መከተል፤ ከጠላት ጋር የመተባበር ሥራ መስራት ነውር እና አጸያፊ ነው፡፡

ለባንዳ አድሮ የሀገርን ጥቅም የሚጎዳ፣ ክብር የሚነካ፣ የሀገርን ህልውና የሚያዳክም እንዲሁም ሌሎች ሀገርን የሚጎዳ ተግባር ውስጥ መገኘት ቀርቶ በሃሳብ ደረጃ መታሰብም እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡

ይህ እንዳይፈጠር ዜጎች ስለሀገር ያላቸው ግንዛቤ ላይ መስራት እና ማስተማር ይጠበቃል በማለት ገልጸው÷ ይህም ሲሆን ባኮረፈ ቁጥር የሚሸፍት ሳይሆን ልዩነት ሲኖረው መንግሥትን በሃሳብ የሚሞግትና የሚጠይቅ ዜጋ መፍጠር ይቻላል ብለዋል፡፡

የሚጠይቅበት መንገድም ከሀገር ጥቅም እና ከሀገር ማንነት ጋር በተዋቀረ ይሆናል ያሉት ተመራማሪው÷ ሀገር ከግል ጥቅም ጋር ብቻ የሚታይ እንዳልሆነ ለመረዳት ግንዛቤ እንደሚያገኝ ጠቁመዋል።

ሀገር ስንኖርና ስንሞት ክብራችን በመሆኗ ከሁሉም በላይ እንደሆነች መረዳት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

በብርሃኑ አበራ

ያዕቆብ አርሳኖ (ፕ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ👇
https://www.youtube.com/watch?v=3gk8SQfUt7Q

Exit mobile version