Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

13 ቢሊየን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተበርክቷል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ለከተማ አስተዳደሩ ከልማት አጋሮች እና ሕዝብ 13 ቢሊየን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተበርክቷል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ከንቲባዋ “በትጋት አዲስ አበባን ወደ ላቀ ስኬት!” በሚል መሪ ሃሳብ ባለፉት ቀናት ስናካሂድ የነበረውን የከተማችንን የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የመንግሥትና የፓርቲ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ በስኬት አጠናቅቀናል ብለዋል።

በግምገማውም አዲስ አበባን ፅዱ፣ አረንጓዴ እና ውብ፤ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ የተከናወኑ አበረታች ውጤቶችን አይተናል ነው ያሉት።

ለአብነትም 134 ኪ.ሜ አዳዲስ መንገዶች የተገነቡ መሆናቸውን ገልጸው÷ ከ573 ኪ.ሜ በላይ መንገዶች ጥገና እንደተደረገላቸው አመልክተዋል።

በውሃና ፍሳሽ ጋር በተያያዘ የውሃ አቅርቦትን በ60 ሺህ ሜትር ኩብ ለማሳደግ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ያሉት ከንቲባዋ÷ የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓቱን በማዘመን ከተማችንን ከብክለት ለመከላከል የ8 ማጣሪያዎች ግንባታ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በትምህርት፣ በጤና እና በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች የህዝቡን አዳጊ ፍላጎት መሰረት ያደረጉ 274 ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በኮሪደር ልማትና በወንዝ ዳርቻ ስራዎችም ከተማችንን መልሰን እየገነባን፣ ከከተማችን አልፈን የሀገራችንን ገጽታ ቀይረናል በማለት ገልጸው÷ ለነዋሪዎቻችን 12 ሺህ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችንም ገንብተን ለተጠቃሚዎች አስተላልፈናል ብለዋል።

የከተማዋ የኮንፍረስ ቱሪዝም መዳረሻነት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንና ባለፉት 6 ወራት ከ150 በላይ ኮንፍረንሶች መካሄዳቸው ጠቁመው÷ በስራ ዕድል ፈጠራ ከ195 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ እና ለበርካቶች በጊዜያዊነት የስራ ዕድል የመፍጠር ስራ መከናወኑን አብራርተዋል።

ከሕዝቡ ቅሬታ ከሚቀርብበት የአገልግሎት አሰጣጥ አንፃርም በ’መሶብ’ የአገልግሎት አሰጣጥ የ94 በመቶ የህዝብ እርካታ ማግኘት መጀመራችን ለቀጣይ ስራችን ትልቅ ስንቅ ነው ሲሉም አክለዋል።

የበጎ ፈቃድ ተሳትፎም በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ከባለድርሻ የልማት አጋሮቻችን እና ከሕዝባችን 13 ቢሊየን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማበርከት ከፍተኛ የሕዝብ አጋርነት የታየበትም ነበር ሲሉም አመልክተዋል።

በቀጣዮቹ 6 ወራትም ትኩረት የሚሹ የአመራር አፈፃፀም ልዩነቶችን በማጥበብ፣ ተቋማዊ ግንባታን ለማጠናከር፣ ጉበኝነትና ብልሹ አሰራርን በዘመናዊ አሰራር እና በሕዝብ ተሳትፎ ለማምከን፣ የመረጃ አያያዝን ለማዘመን እንዲሁም የኑሮ ውድነትን ጫና ለመቀነስ የተጀመሩ ስራዎችን ለመቀጠል የገቢ አሰባሰብን አጠናክረን ለመስራት የተግባቡበት ውጤታማ መድረክ እንደነበርም ጠቁመዋል።

Exit mobile version