Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስፋፋት የባለሙያ፣ ቴክኖሎጂ እና መሰረተ ልማት የማሟላት ስራዎች በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ።

የቢሮው ኃላፊ መለሰ በየነ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ኢኒሼቲቭ በክልሉ መልካም ውጤቶችን እያሳየ ይገኛል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች የመልካም አስተዳደር ስብራት እንዲያጋጥም ማድረጉን አንስተው÷ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ክልሉ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስጀመር ማሕበረሰቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ መጀመሩን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ከተጀመረ በኋላም በርካታ የማሕበረሰብ ክፍሎች ወደ ተለያዩ ቦታዎች መሄድ ሳያስፈልጋቸው በመሶብ አንድ ማዕከል ከስምንት በላይ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ተገልጋዮች የሚፈጅባቸውን ጊዜ በማሳጠር ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት በመቻላቸው መልካም የሆነ ግብረ መልስ እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቅሰው÷ ይህም በመንግሥት እና ሕዝብ መካከል ጥሩ ግንኙነት እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።

አገልግሎቱን በክልሉ በሚገኙ ከተማ አስተዳደሮች እንዲስፋፋ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አንስተው÷ የባለሙያ፣ ቴክኖሎጂ እና መሰረተ ልማትን የማሟላት ስራዎች በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በአሶሳ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ስራዎች እየተጠናቀቀ መሆኑን እንዲሁም በግልገል በለስ ከተማ አስተዳደር አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተከናወኑ እንደሆነና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በክልሉ በሚገኙ ሌሎች ከተማ አስተዳደሮች የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲስፋፋ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው÷ ሁሉም ባለድርሻዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version