Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ማርበርግን በመቆጣጠር ረገድ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን የመከላከል ስልት ተግብራለች – ርዕሳነ መስተዳድሮች

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማርበርግ ቫይረስን በመቆጣጠር ረገድ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን የበሽታ መከላከል ስልት ተግብራለች አሉ የደቡብ ኢትዮጵያና ሲዳማ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፡፡

በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ቫይረስ ከወራት በኋላ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉን ተከትሎ የእውቅና መርሐ ግብር ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው አካላት በቁርጠኝነትና በትብብር መስራታቸው አመርቂ ውጤት እንዲመዘገብ አስችሏል፡፡

መንግሥት ፈተናዎችን ወደ እድል የመቀየር ባህል እንዳለው ገልጸው÷ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከሕዝብ ጋር በመስራት በዘርፉ አበረታች ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል፡፡

የማርበርግ ቫይረስ ሲከሰት በመናበብ ፈጣን ምላሽ መስጠታችን የውጤታማነታችን ማሳያ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷በሕዝቦች፣ በጤና ባለሙያዎችና በአመራሩ ቁርጠኝነት ውጤት መመዝገቡን አውስተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ በሽታ በፍጥነት ነፃ መሆኗ ባለፉት ሰባት ዓመታት በጤና ተቋማት ግንባታ ላይ የታየው ስኬት ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን ለማጥፋት የወሰደችው ርምጃ ያላትን ጠንካራ የጤና ፖሊሲ በተግባር የገለጠ መሆኑን ጠቅሰው÷ማህበረሰቡም ተገቢ ምላሽ የሰጠበት ነው ብለዋል፡፡

የማርበርግ ቫይረስ የተሰጋውን ያህል ጉዳት ሳያደርስ በቀላሉ ማጥፋት ተችሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ለዚህ ደግሞ የጤና ተቋማት ቅንጅት የላቀ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ርዕሳነ መስተዳድሮች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን የበሽታ መከላከል ስልት ገቢራዊ ማድረጓን ገልጸው÷ ለዚህ ስኬት አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡

Exit mobile version