አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በማልማት ስራ የተደራጁ ማሕበራት ባለፉት 6 ወራት ብቻ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል አለ የአዲስ አበባ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ።
የፕላስቲክ ከረጢቶች እና ጠርሙሶች በተፈጥሮ በቀላሉ የማይበሰብሱ በመሆናቸው በአግባቡ ካልተወገዱ የአካባቢ ሥነ ምሕዳር እንዲዛባ በማድረግ በሰው ልጅ ጤና፣ በእንስሳት እና በእጽዋት ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሳሉ።
በመዲናዋ ደረቅ ቆሻሻን በማጽዳት እና መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ አካባቢ ከብክለት ነጻ እንዲሆን የሚያስችሉ ስራዎችን የአዲስ አበባ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በማከናወን ላይ ይገኛል።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሙላት ተገኘ እንዳሉት÷ የተለያዩ ደረቅ ቆሻሻዎች በወንዞች እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ እየተጣሉ አካባቢዎችን ሲበክሉ እንደነበር አስታውሰዋል።
ነገር ግን የጽዳት ሥራ ከተጀመረ ወዲህ ደረቅ ቆሻሻዎች በአግባቡ የሚሰበሰቡበት እና አካባቢን የማይበክሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በማልማት ሥራ ዙሪያ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህም ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ4 ሺህ በላይ ዜጎች ከ400 በላይ በሚሆኑ ማሕበራት በመደራጀት በዘርፉ ተሰማርተው ይገኛሉ ያሉት አቶ ሙላት ÷ ገቢ እያገኙ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ እነዚህ ማህበራት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የሚሆን ገቢ ማግኘታቸውን ነው ያብራሩት።
በተጨማሪም የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ወደ አዲስ ምርት በመቀየር ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች የገበያ ትስስር እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዮናስ ጌትነት

