Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከ2010 የዓለም ዋንጫ በኋላ ምርጥ ብቃቱ የከዳው ቶሬስ…

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም እግር ኳስ ከተመለከታቸው ምርጥ የፊት መስመር ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው የስፔን ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ኮከብ ፈርናንዶ ቶሬስ፡፡

ቶሬስ በተጫዋችነት ዘመኑ ከምርጥ አጥቂዎች መካከል አንዱ የነበረ ሲሆን÷ በፍጥነቱ፣ በጎል አስቆጣሪነቱ እና በድንቅ ችሎታው ይታወቃል፡፡

ፈርናንዶ ቶሬስ ለተከላካዮች ፈታኝ ከመሆኑ ባለፈ ጥንካሬው፣ ፍጥነቱ፣ ጉልበቱና የአጨራረስ ብቃቱ አስገራሚ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ቶሬስ ወደ አንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በመጣበት በመጀመሪያው የውድድር ዓመቱ በ33 የሊጉ ጨዋታዎች 24 ግቦችን ለሊቨርፑል ማስቆጠር ችሏል፡፡

በወቅቱ ሊቨርፑል እንደ ቡድን ደካማ ቢሆንም ቶሬስ ግን በአንፊልድ በነበረው ቆይታ በግሉ ምርጥ ብቃት ላይ ነበር፤ከሊቨርፑል በተጨማሪም ለአትሌቲኮ ማድሪድ፣ ቼልሲ እና ኤሲሚላን ተጫውቶ አሳልፏል፡፡

ተጫዋቹ ከምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ጋር የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ፣ ዩሮፓ ሊግ እና የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ማሳካቱ አይዘነጋም፡፡

በቼልሲ በነበረው ቆይታ ከቡድኑ ጋር ዋንጫዎችን ያሳካ እንጂ በሊቨርፑል ያሳየውን ምርጥ ብቃት ግን ማስቀጠልና ማጠናከር አልቻለም ነበር፡፡

ፈርናንዶ ቶሬስ ዋናውን የስፔን ብሔራዊ ቡድን ከፈረንጆቹ 2003 ጀምሮ እስከ 2014 ድረስ ያገለገለ ሲሆን÷ በ2010 የዓለም ዋንጫን አሳክቷል፡፡ለስፔን ብሄራዊ ቡድን ባደረጋቸው 110 ጨዋታዎች 38 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከሀገሩ እና ከክለብ ስኬቶቹ በተጨማሪ በግሉ በፈረንጆቹ 2008 በባሎንዶር የሽልማት ሥነ ሥርዓት 3ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቀ÷ በዚያው ዓመት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የዓመቱ ምርጥ 11 ውስጥ ለመካከተት በቅቷል፡፡

በፈረንጆቹ 2008 እና 2009 ደግሞ የፊፋ የዓመቱ ምርጥ 11 ውስጥ የተካተተው ቶሬስ÷ የማይረሱ ውብ ትዝታዎችን በሊቨርፑል ቤት በማስቀመጥ እና በፕሪሚየር ሊጉ ከታዩ ምርጥ 9 ቁጥር ለባሽ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆኑን አሳይቷል፡፡

በሊቨርፑል ማልያ ደምቆ በቆየባቸው አራት ዓመታት ተከላካዮች እሱን ለማቆም ይቸገሩ ነበር፡፡በአንድ ወቅት ቶሬስ “እኔ ጎል አስቆጥራለው፤ ሊቨርፑል አያሸንፍም ፤ሊቨርፑል ዋንጫ ሊበላ አይችልም፤ስለ ዋንጫ አያስብም” በማለት አስተያየቱን ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በሊቨርፑል ቤት ባሳየው አቋም የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ቶሬስ ከ2010 የዓለም ዋንጫ ውድድር በኋላ በምርጥ ብቃቱ መቀጠል አልቻለም ፡፡

በፈረንጆቹ 2011 አንፊልድን በመልቀቅ ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ ቢያቀናም በምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ የተጠበቀውን ያህል ብቃቱን ማሳየት አልቻለም፡፡

ቶሬስ በእግር ኳስ ዘመኑ መጨረሻ ወደ ጃፓን ሊግ አቅንቶ ለሁለት የውድድር ዓመት ያህል ከተጫወተ በኋላ በፈረንጆቹ 2019 ጫማውን መስቀሉ ይታወሳል፡፡

ከዚያ በኋላ ከ2021 እስከ 2024 ድረስ የአትሌቲኮ ማድሪድን ከ19 ዓመት በታች ቡድን ያሰለጠነ ሲሆን ÷ በአሁኑ ወቅት ደግም የአትሌቲኮ ማድሪድ ቢ ቡድንን በአሰልጣኝነት እየመራ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

Exit mobile version