አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ለውጪ ገበያ ካቀረበቻቸው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ምርቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና ፓርኮች ውስጥ የተመረቱ ናቸው አለ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፡፡
በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ በለጠ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጵያ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 204 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ለውጪ ገበያ አቅርባለች።
ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች አምርተው ለውጪ ገበያ ካቀረቡት ምርቶች ከ112 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ጠቁመዋል።
ይህም የሀገራዊ አፈጻጸሙን 55 በመቶ እንደሚሽፍን ገልጸው፥ ባለፉት 6 ወራት ለሀገር ውስጥ ገበያ የቀረበው የምርት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ61 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ከ13 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ምርት ኮርፖሬሽኑ ከሚስተዳድራቸው ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና ፓርኮች ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች አምርተው ለሀገር ውስጥ ገበያ አቅርበዋልም ነው ያሉት።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከ161 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ከ85 ሺህ በላይ የሚሆነው የስራ ዕድል የተፈጠረው በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ባለፉት 6 ወራት ብቻ 74 ድርጅቶች 4 ሺህ 800 በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ዘላቂ የሆነ ተጨማሪ የገበያ ትስስር መፍጠር መቻላቸውን አመልክተዋል።
በተፈጠረው የገበያ ትስስርም ከ6 ቢሊየን ብር በላይ ግብይት መፈጸም ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በአድማሱ አራጋው

