አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጊፋታ እሴቱን ጠብቆ የሕዝቦችን አንድነት ይበልጥ እንዲያጠናክር በትኩረት መስራት ያስፈልጋል አሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ።
የወላይታ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ጊፋታ” በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡን ተከትሎ ሀገራዊ የደስታ ማብሰሪያ መርሐ ግብር በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።
አቶ ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅት ጊፋታ የተጣሉ የሚታረቁበት ከበዓል ያለፈ ጥልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ለክልሉ ቱሪዝም እና ኢኮኖሚ ተጨማሪ ስራ እድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው÷ የቱሪዝም ዘርፉን እመርታ ለማስፋት፣ ለሀገር ገጽታ ግንባታ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ባህልን ከቱሪዝም ልማት ጋር በማስተማር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው÷ ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና የሕዝቦች አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአብሮነት የተጋመደ በርካታ ተፈጥሯዊ ሃብት እንዳላት ገልጸው÷ ጊፋታ የዓለም ሕዝቦች አኩሪ ባህል ሆኗል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ሰባት ቅርሶች በዩኔስኮ መመዝገባቸውን ጠቅሰው÷ በሀገራችን ያሉ ባህሎች ለሀገራችን ብልጽግና የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ ብለዋል።
ቅርሶችን በማስመዝገብ፣ በማስተዋወቅ እና በማልማት ኢኮኖሚን በማመንጨት ላይ መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በሀገሪቱ የሕዝብ ትስስር፣ አንድነትና መከባበር ላይ መሰረት ያደረጉ በርካታ ባህሎች መኖራቸውን ገልጸው÷ ጊፋታ ለማህበራዊ እሴቶች የሚያበረክተው አሰተዋጽኦ የላቀ ነው ብለዋል።
ለሁለንተናዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን ባህሎች በመጠበቅ ለሕዝቦች አንድነትና እድገት በትጋት መስራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የማብሰሪያ መርሐ ግብሩ “የጊፋታ ብስራቶች ለሕዝቦች ከፍታ” በሚል መሪ ሐሳብ የተካሄደ ሲሆን÷ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የብሔረሰቡ ተወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በማቴዎስ ፈለቀ

