Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አየር ኃይል ባከናወናቸው የሪፎርም ተግባራት በአይነተኛ የለውጥ መንገድ ላይ ይገኛል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ባከናወናቸው የሪፎርም ተግባራት በአይነተኛ የለውጥ መንገድ ላይ ይገኛል አሉ።

አየር ኃይሉ ለሶስት ዓመታት የሰለጠኑ አብራሪዎች፣ እጩ መኮንኖች እና ቴክኒሻኖችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አየር ኃይል በየዘመናቱ የሚሸረቡ የጠላት ሴራዎችን ሲያከሽፍ ቆይቷል ብለዋል።

ተቋሙ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ባከናወናቸው የሪፎርም ተግባራት በስኬት ታጅቦ 90ኛ ዓመቱን ማክበሩን ጠቁመው፤ ክብረ በዓሉ ያስመለከተን እውነቶች ተወዳዳሪ አቪዬሽን መገንባት መቻላችንን አረጋግጦልናል ነው ያሉት፡፡

አየር ኃይሉ ባከናወናቸው የሪፎርም ተግባራት በአይነተኛ የለውጥ መንገድ ላይ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ መሰረተ በማድረግ በመሰረተ ልማትና በሰው ኃይል ራሱን ሲያበቃ መቆየቱን አረጋግጠዋል።

የዛሬ ተመራቂዎች የተቋሙን ዝግጁነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ያሸጋግራሉ በማለት ገልጸዋል።

የዓለም የጦርነት አውድ ተለዋዋጭ፣ ፉክክርና ፈጣን እድገት እንደሚስተዋልበት ጠቅሰው፤ የጦርነት አውዱ ከነጠላ ውጊያ ወደ ዘርፈ ብዙ የጦርነት አውድ ተሸጋግሯል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ ከአካዳሚና ከበረራ ስልጠና ጎን ለጎን ለሀገራቸውና ለተቋማቸው የታመኑ እንዲሆኑ አድርጎ በማነጽና በማብቃት ሲያስመርቅ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡

የኢፌዴሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነትና አንድነት ምልክት” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ከጥር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።

በመራኦል ከድር

Exit mobile version