Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ የተገነባውን ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀዝቀዣ መጋዘን መረቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ያስገነባውን ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ማቀዝቀዣ መጋዘን እና ሁለገብ ሕንጻ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ከ11 ሺህ 400 ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ ላይ ያረፈና በሀገሪቱ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው የማቀዝቀዣ መጋዘንና ሁለገብ ሕንፃ ከምርት በኋላ የሚፈጠርን ብክነትና ብክለት ያስቀራል፡፡

በዚህም የገበያ ማረጋጋትን በመፍጠር እንዲሁም በአምራቹ የሚመረቱ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦዎች ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ለሸማቹ ማሕበረሰብ እና ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድ የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ሸማቹ ማሕበረሰብ በተገቢ ዋጋ ትኩስ የግብርና ምርቶችን እንዲያገኝ የሚያስችል ሲሆን÷ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የገበያ ሰንሰለቱን በማሳጠር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ጠቅሰዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ለግብርና ምርት ጥራትና ተወዳዳሪነት አስፈላጊ የሆነው ይህ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ይዞታ በማቅረብ ያደረገውን ድጋፍ በሌሎችም ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በዘርፉ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ከፍተኛ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ተቋማት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

በተካልኝ ኃይሉ

Exit mobile version