አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በንግድ ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በአሰራር ለማረም የተከናወነው ሥራ መሰረታዊ ለውጥ እያመጣ ነው አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)።
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ያስገነባው ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ማቀዝቀዣ መጋዘንና ሁለገብ ሕንጻ ተመርቆ ለስራ ክፍት ተደርጓል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ መጋዘኑ በአንድ ጊዜ 20 ሺህ ኩንታል በላይ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦን የማቀዝቀዝና 10 ሺህ ኩንታል የማደራጀት አቅም አለው፡፡
በ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀዝቀዣ መጋዘኑ ÷ በ11 ሺህ 400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ማረፉን አመልክተዋል፡፡
በንግድ ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በአሰራር ለማረም የተከናወነው ሥራ መሰረታዊ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት፡፡
የኢትዮጵያን ንግድ ሥነ ምህዳር ለማዘመንና በዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይም መሰረታዊ ሸቀጦችን በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ፣ የገበያ ትስስርን ለማጠናከርና ንግድን የሚያሳልጡ ዘመናዊ ሎጂስቲክሶችን ለማስፋፋት ትኩረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ÷ ለአብነትም የስንዴ ምርትን ወደ ውጪ በመላክ ረገድ ያስገኘውን ስኬት አብራርተዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተቋሙ እየሰራ ያለውን ሥራ የሚመሰገን ነው ያሉት ሚኒስትሩ ÷ ለተሻለ ውጤት መትጋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በተካልኝ ኃይሉ
👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ፡-

