Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከ359 ሺህ ቶን በላይ ማር ለማምረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ ከ359 ሺህ ቶን በላይ ማር ለማምረት እየተሰራ ነው አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡

በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደ ሀገር ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ትኩረት ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል የንብ ማነብ ስራ ይገኝበታል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ግርማ ሙሉጌታ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ የማር ምርታማነትን ለማሳደግ እና ጥራቱን ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ባህላዊ የንብ ቀፎዎችን በዘመናዊ ቀፎ ለመተካት ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ንብ አናቢዎች ዘመናዊ ቀፎዎችን ምርጫቸው እያደረጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ዘንድሮ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለማሰራጨት ዕቅድ መያዙን ጠቅሰው÷ በመጀመሪያ ስድስት ወራት አመርቂ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች እየተሰራጩ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡

ባለፈው ዓመት 326 ሺህ ቶን ማር እንደተመረተ አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት ምርቱን ከ359 ሺህ ቶን በላይ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የማር ምርት አቅም ያላቸው አካባቢዎች ተለይተው በመንደር መደራጀታቸውን ገልጸው፤ ይህም ንቦች የሚቀስሙት አበባ እንዲያገኙና አደጋ ሊያደርሱባቸው የሚችሉ ነገሮችን ለመከላከል እንዲሁም ቴክኖሎጂን በቀላሉ ለማድረስ ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት፡፡

 

ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ8 ሺህ 800 በላይ የማር መንደሮች መመስረታቸውን አስረድተዋል።

 

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version