አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው የመላ አፋር ስፖርት ውድድር “አንድነት ለጥንካሬያችን ስፖርት ለሠላማችን” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው፡፡
በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ማህበራዊ ጉዳዮች አስተባባሪና የባህል፣ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሐሚድ ዱላ እንዳሉት÷ ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት ያስችላል፡፡
በፈንቲ ረሱ እየተካሄደ የሚገኘው ውድድሩ ÷ መከባበር፣ መቻቻል እና አብሮነትን የሚያንጸባርቅ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው ÷ ክልሉ ለስፖርቱ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ለመርሐ ግብሩ ያደረገው ዝግጅት የአመራሩን ጥንካሬ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የለውጡ መንግሥት ለስፖርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ መሐመድ አህመድ ዓሊ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

