Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ባንኮች እርስ በርስ የውጭ ምንዛሪ ግብይት የሚያካሂዱበት ዲጂታል አውታር ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባንኮች እርስ በርስ የውጭ ምንዛሪ ግብይት የሚያካሂዱበት ዲጂታል አውታር በይፋ ስራ ጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ፣ የንግድ ባንኮችና የፋይናንስ ዘርፉ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የግብይት አውታሩ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ላለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና ለፋይናንስ ዘርፍ ዘመናዊነት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑ ተገልጿል።

በባንኮች መካከል በሚደረገው የውጭ ምንዛሪ ገበያ ውስጥ ግልጽነትን፣ ትክክለኛ ዋጋን የማወቅ ሂደትን እና የገበያ ሥርዓትን ያጠናክራል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በይፋ ስራ የጀመረው ዲጂታል የግብይት አውታር የሀገራችን የውጭ ምንዛሪ ገበያን መዋቅር ለማዘመን አስፈላጊ እርምጃ መራመዳችንን ያሳያል ብለዋል።

አውታሩ ለተሳታፊ ሁሉ ግልጽ፣ ፈጣንና በመመሪያ የተመራ የገበያ ከባቢ ይፈጥራል ነው ያሉት።

መድረኩ የገበያ ዲሲፕሊንን ለማጠንከር፣ የዋጋ ሂደትን ለማሻሻልና የፋይናንስ ገበያ ሪፎርምን ለመደገፍ ትልቅ ግብዓት ነው ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

ሁሉም ባንኮች በመድረኩ ላይ በንቁ መንገድ እንዲሳተፉ እና ከመመሪያዎች ጋር የተጣጣመ ሥራ እንዲያከናውኑም አሳስበዋል።

Exit mobile version