Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ጋር የተጣጣመው የዲጂታላይዜሽን ጉዞ በኦሮሚያ ክልል…

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጋር በተጣጣመ መልኩ የዲጂታላይዜሽን ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ ነው አለ የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለስልጣን፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መኮንን በየነ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ በክልሉ በሁሉም ዘርፍ ዲጂታላይዜሽንን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
በተለይም የመሬት አስተዳደር ዘርፉ ሙሉ ለሙሉ ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ በዲጂታል ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የዲጂታል መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት የክልሉ መንግስት በስፋት እየሰራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፥ ዲጂታላይዜሽን ብልሹ አሰራርና ሙስናን በማስቀረት ለኢኮኖሚው ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል፡፡
ይህንን ከፍተኛ ሚና ለሕብረተሰቡ በማስገንዘብ ረገድ ተከታታይ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፥ በዚህም ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በከተሞች የሚኖረውን አብዛኛውን ማህበረሰብ የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ማድረግ መቻሉንና የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
የተቋማትን አገልግሎት ወደ ዲጂታል ስርዓት ማስገባት ከሙስና እና ብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር ያስችላል ያሉ ሲሆን፥ ሕብረሰተቡ ይህንን በመገንዘብ ዲጂታል ስርዓቱን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም በተቋማት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በመከወንና የሰው ኃይሉን በዲጂታል ክህሎት ለማብቃት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በአቤል ነዋይ
Exit mobile version