አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጅምናስቲክ ስፖርት ተወዳዳሪው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ድሪባ ቶሌራ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስፖርት ፌስቲቫል ላይ ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል፡፡
በስፖርት ፌስቲቫሉ በትናንትናው ዕለት ፍፃሜውን ባገኘው የጅምናስቲክ ውድድር አስተናጋጁ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በ76 ነጥብ 1ኛ በመሆን የቡድን ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል::
የዩኒቨርሲቲው የሲቪል ምህንድስና 2ኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ድሪባ ቶሌራ በተወዳደራባቸው የጅምናስቲክ የስፖርት አይነቶች አራት የወርቅና አንድ የብር ሜዳልያዎችን አሳክቷል፡፡
በተጨማሪም ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን ዩኒቨርስቲውን የዋንጫ ባለቤት ማድረግ ችሏል፡፡
በተወዳደረበት የጅምናስቲክ ውድድር ባገኘው ስኬት መደሰቱን ገልጾ፥ በቀጣይ በኦሊምፒክና በሌሎች ውድድሮች ሀገሩን የመወከል ህልም እንዳለው ተናግሯል፡፡
ከተሳትፎም ባሻገር በዓለምአቀፍ መድረክ ለሀገሬ ሜዳልያ የማስገኘት ፍላጎት አለኝ የሚለው ተማሪ ድሪባ፥ ለዚህም አቅሙን በተሻለ ስልጠና ማገዝ የሚችልበት እድል እንዲመቻችለት ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስፖርት ፌስቲቫል በ15 የስፖርት አይነቶች በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት በድምቀት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በተስፋሁን ከበደ

