ማይክሮ አልጌ (ስፓይሮሊና) የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር ለጤና ያለውን ጠቀሜታ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዮት ብርሀኑ እንዳሉት÷ የስፓይሮሊና ምርቶች ለብዝሀ ሕይወት ጥበቃ እና ለሕብረተሰብ ድጋፍ ለማዋል በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው፡፡ማይክሮ አልጌ የሥርዓተ ምግብ ተግዳሮቶችን ከመቅረፍ አንፃር ያለው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ ባካሄደው ጥናት ማረጋገጡን አመልክተዋል፡፡
በተለይም ስፓይሮሊና የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር ለጤና ያለውን ጠቀሜታ ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት አየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል
ለአብነትም የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ማይክሮ አልጌን በሳይንሳዊ መንገድ አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ከኢቲኬር የውበት መጠበቂያ ምርቶች ሽያጭ ኃላፊነቱ የተ/የግ/ማህበር ጋር መፈራረሙን ተናግረዋል፡፡
ለንግድ ዓላማ የሚውሉ ከ35 በላይ ስምምነቶች የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ማድረጉን ጠቁመው÷ ይህም ለኢንስቲትዩቱ ትልቅ ግብ መሆኑና የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአግባቡ ያልተጠቀመችባቸው በርካታ የተፈጥሮ ሐብቶች እንዳሏት የገለፁት ም/ዋና ዳይሬክተሩ÷ ከእነዚህ መካከል አልጌ አንዱ መሆኑንና ከኢቲኬር ጋር የተደረገው ስምምነት ዘርፉን ወደላቀ ደረጃ ሊያደርስ የሚችል ነው ብለዋል።
የተደረገው ስምምነት ከአልጌ የሚዘጋጁ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የውበት መጠበቂያ ምርቶች ማምረትን እንደሚያካትት ተመላክቷል፡፡
http://ማይክሮ አልጌ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር ለጤና ያለውን ጠቀሜታ ለማሳደግ..

