አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጫዋችነት ዘመኑ በእግር ኳስ ችሎታው ብዙዎችን ያስገረመ ተጫዋች ነው የቀድሞ የማንቼስተር ዩናይትድ ተጫዋች ቤርባቶቭ፡፡
የቀድሞ የቡልጋሪያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ቤርባቶቭ አፍን በእጅ በሚያስጭን የመጀመሪያ የኳስ ንክኪው የሚታወስ ድንቅ ኮከብ ነው፡፡
ቤርባቶቭ ከእግር ኳስ ችሎታው ባለፈ መልካም ባህሪው ያለው ስለመሆኑ ብዙዎች መስክረውለታል፡፡
የኳስ ችሎታው በግርምት አፍን የሚያስይዝ በመሆኑ የእግር ኳስ ቤተሰቦች ስለ መጀመሪያ የኳስ ንክኪው ውበት ሲገልጹ 10 ኳስ በአንዴ ቢሰጠው አስሩንም ይቆጣጠራቸዋል በማለት አሞካሽተውታል፡፡
ቤርባቶቭ ለባየር ሊቨርኩሰን፣ ቶተንሃም ሆትስፐር፣ ፉልሃምና ሞናኮ ለመሳሳሉ ክለቦች ተጫውቶ ቢያሳልፍም በስኬት የታጀቡ ዓመታትን ያሳለፈው በማንቼስተር ዩናይትድ ነው፡፡
በርካታ የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች በችሎታው ተገርመው ሊያስፈርሙት ቢፈልጉም፥ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በአንድ የስልክ ጥሪ ወደ ኦልድ ትራፎርድ ሊያመጡት ችለዋል፡፡
ፈርጉሰን ቤርባቶቭ ጋር ስልክ በመደወል እፈልግሀለው እኔ ጋር ና እንዳሉት ተጫዋቹ በአንድ ወቅት መናገሩ አይዘነጋም፡፡
ጊዜውን ሲያስታውስ ሰር አሌክስ ፈርጉሰንን በስልክ ካወራሁበት ሰዓት ጀምሮ ማንቼስተር ዩናይትድን የመቀላቀሌ ነገር ገና ድርድሩ ሳይጀመር ማለቁን ለራሴ ወዲያው ነበር ያሳመንኩት ሲል ቤርባቶቭ ተናግሯል፡፡
የማንቼስተር ዩናይትድ ጥሪ ሲደርሰው ወደ ኦልድትራፎርድ ለመሄድ ከመጓጓቱ የተነሳ የቶተንሀም ሆትስፐር ጓደኞቹን ለመሰናበትም ጊዜ አልነበረውም፡፡
በፈረንጆቹ 2008/9 የውድድር ዓመት ማንቼስተር ዩናይትድን የተቀላቀለው ተጫዋቹ በኦልድትራፎርድ በነበረው ቆይታ በዋንጫ የታጀቡ ዓመታትን አሳልፏል፡፡
ቤርባቶቭ ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር ሁለት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ አንድ የዓለም ክለቦች እና ሁለት የኮሚኒቲ ሺልድ ዋንጫዎችን ማሳካት ችሏል፡፡
በ2010/11 የውድድር ዓመት ማንቼስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድ ትራፎርድ ብላክበርን ሮቨርስን 7 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ቤርባቶቭ አምስት ግቦችን ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡
በዚህም በፕሪሚየር ሊጉ በአንድ ጨዋታ አምስት ግብ ያስቆጠረ እንግሊዛዊ ያልሆነ የመጀመሪያው ተጫዋች በመሆን አዲስ ክብረወሰን መያዝ ችሎ ነበር፡፡
በ2010/11 የውድድር ዓመት በሊጉ 20 ግቦችን በማስቆጠር የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የወርቅ ጫማ አሸናፊ መሆኑ አይዘነጋም፡፡
ቤርባቶቭ በ2007፣ 2008 እና 2010 በፊፋ የዓመቱ ምርጥ 11 ውስጥ መካተት የቻለ ተጫዋች ነው፡፡
ቤርባቶቭ ለሀገሩ ቡልጋሪያ 78 ጨዋታዎችን አድርጎ 48 ግቦችን በማስቆጠር የብሔራዊ ቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው፡፡
ተጫዋቹ በእግር ኳስ ዘመኑ መጨረሻ ለግሪኩ ፓኦክ እና ለሕንዱ ኬራላ ብላስተርስ ከተጫወተ በኋላ በፈረንጆቹ 2019 ራሱን ከተጫዋችነት ማግለሉ ይታወሳል፡፡
በማንቼስተር ዩናይትድ ቤት በስኬት የታጀቡ ዓመታትን ያሳለፈው ቤርባቶቭ በፈረንጆቹ 1981 በዛሬዋ ዕለት ነበር የተወለደው፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ

