አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቡና ሀብትን የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ለማድረግ በትኩረት መስራት ይገባል አለ የቱሪዝም ሚኒስቴር።
ሀገር አቀፍ የቡና ቱሪዝም ሴሚናር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም መስህብ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ ሙሳ ከድር በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በሀገሪቱ ከተለመዱ መዳረሻዎች ውጪ ያልታዩና ያልተዳሰሱ እምቅ ሀብቶችን ወደ ገበያ በማቅረብ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።
ኢትዮጵያ ከቡና ጋር የታሪክና የባሕል ቁርኝት ያላት ሀገር መሆኗን በማንሳት÷ በዘርፉ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በየአካባቢው የሚገኙ ሀብቶችን የመለየት፣ የማስተዋወቅ እና የማልማት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው÷ የቡና ሀብት የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የቡና ቱሪዝምን ዕውን ለማድረግ አምራች ዩኒየኖች፣ ማህበራት፣ የቡና ላኪዎች፣ አስጎብኚዎች እና በዘርፋ ላይ እየሰሩ የሚገኙ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ግንዛቤ መፍጠር ላይ የበለጠ ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት።
የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አበበ ማረሞ በበኩላቸው÷ ቡናን ወደ ውጭ ከመላክ ባሻገር የቡና ቱሪዝምን በማስፋት ከጎብኚዎች የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚቻል አንስተዋል።
በብርሃኑ በጋሻው

