አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ፍርድ ቤት በህገ ወጥ መንገድ ነዳጅ ያጓጓዘ አሽከርካሪ በእስራት እና በገንዘብ እንዲቀጣ ወሰነ።
ፍርድ ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት ባሳለፈው ውሳኔ እንዳመለከተው፤ ተከሳሹ አሽከርካሪ ክፍሌ ዋቁማ በጅማ ዞን ባልተፈቀደለት አግባብና አቅጣጫ በቦቴ ነዳጅ ጭኖ ሲያጓጉዝ ተገኝቷል።
አሽከርካሪው ግምቱ 5 ሚሊየን 207 ሺህ 902 ብር የሆነ 46 ሺህ 649 ሊትር ናፍጣ ከጅቡቲ ወደ ጋምቤላ ለማጓጓዝ ህጋዊ ደብዳቤ ቢይዝም፥ የተፈቀደለትን የጋምቤላ መስመር በመተው በጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ በኩል አቋርጦ ወደ ቦንጋ እየተጓዘ ሳለ ጥቅምት 29 ቀን 2018 ዓ.ም በህግ ቁጥጥር ስር ውሏል።
በዚህም በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በ2 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ እንዲሁም ነዳጁ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን መወሰኑን የጅማ ዞን ዐቃቤ ህግ ጽ/ቤት ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጿል።
በአብዱራህማን መሃመድ

