Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፖለቲካ ፓርቲ የአይሲቲ ባለሙያዎች ዕጩዎቻቸውን በኦንላይን መመዝገብ ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአይሲቲ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ድጋፍ ዕጩዎቻቸውን በኦንላይን መመዝገብ ጀምረዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ ÷ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባን በምርጫ የጊዜ ሠሌዳው መሠረት ከጥር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡

ቦርዱ ቀደም ሲል ባሳወቀው መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ሥርዓት ታግዘው በመመዝገብ ላይ መሆናቸውንም አስረድቷል፡፡

ምዝገባውን በዲጂታል ሥርዓት ማከናወን እንዲችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሲስተም አስተዳዳሪ ወኪሎቻቸውን ለቦርዱ አሳውቀው በሁለት ዙር ለአራት ቀናት ሥልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል ነው ያለው፡፡

ሥልጠናውን ከመስጠት በተጨማሪ በስልክ እንዲሁም የሲስተም አስተዳዳሪዎችን ያካተተ ቴሌግራም ግሩፕ በመክፈት በምዝገባ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጥያቄዎችን ሲያስተናግድ መቆየቱን ጠቅሷል።

ከዛሬው ዕለት ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት ደግሞ የፓርቲ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በምርጫ ቦርድ ዋናው መሥሪያ ቤት በአካል ተገኝተው በቦርዱ የአይሲቲ ባለሙያዎች ቀጥተኛ ዕገዛ እየተደረገላቸው ዕጩዎቻቸውን እየመዘገቡ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡

እስካሁን 41 በተናጠል እና 15 በሦስት የተለያዩ ጥምረቶች የቀረቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለምዝገባ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን አሟልተው በሲስተሙ ላይ ዕጩዎቻቸውን መመዝገብ የሚያስችላቸው አካውንት ተከፍቶላቸው ዕጩዎቻቸውን በመመዝገብ ላይ ናቸው ብሏል።

በዲጅታል ሥርዓት የታገዘው የዕጩዎች ምዝገባ ባለፉት ምርጫዎች ወቅት ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ክልል ጽ/ቤት በመቅረብ ዕጩዎችን ሲያስመዘግቡ የደረሱባቸውን ችግሮችን ለመቅረፍ እና ከተፅዕኖ ነፃ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ሥርዓቱ በዕጩዎች አመዘጋገብ ወቅት የሚከሰቱ የመረጃ አደረጃጀትና አያያዝ ችግሮችን በመፍታት ፓርቲዎች በራሳቸው “የሲስተም አስተዳደሪ” አማካኝነት ቢሯቸውን ጨምሮ በተመቻቸው ሥፍራ ያለሰዓት ገደብ አንዲመዘግቡ የሚያስችል ነው፡፡

እንዲሁም በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የዕጩዎች አደራደር ቅደም ተከተልን ለመወሠን በሚደረግ የዕጣ አወጣጥ ሥርዓት ወቅት መረጃቸውን እንደ አዲስ ማስመዝገብ ሳያስፈልጋቸው ከሲስተሙ ላይ ዕጣውን ለማውጣት የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

Exit mobile version