Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፀጥታ ሁኔታን ለመገምገም ያለመ መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ለመገምገም ያለመ መድረክ እየተካሄደ ነው።

መድረኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከባለድርሻዎች ጋር የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ያዘጋጀው መሆኑ ተመላክቷል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ከጥር 1 ጀምሮ እስከ የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም በሚቆየው የዕጩዎች ምዝገባ እስካሁን 41 በተናጠል እና 15 በሦስት የተለያዩ ጥምረቶች የቀረቡ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን በመመዝገብ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ምርጫው በሚደረግባቸው አካባቢዎች ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የተለየ ሲሆን÷ በመድረኩ እነዚህ የፀጥታ ሪፖርቶች ቀርበው ከባለድርሻ አካላት ግብአት ይሰጥባቸዋል ብለዋል።

የፀጥታ ሁኔታ ተለዋዋጭ እንደመሆኑ በአንድ መድረክ ብቻ እንደማይቋጭ የጠቀሱት ሰብሳቢዋ÷ በየጊዜው በሚኖሩ አዳዲስ ሁኔታዎች ተመስርቶ ለምርጫው የሚደረገው ዝግጅት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የፀጥታ አካላትና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተገኝተዋል።

በአንዷለም ተስፋዬ

Exit mobile version